የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ካቢኔ ከእስራኤል ጋር የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አፀደቀ
የእስራኤል ክኔሴት (ፓርላማ) ስምምነቱንባለፈው ሳምንት አጽድቋል
ስምምነቱ የቀጣናውን ህዝቦች የብልፅግና እና የለውጥ መሻት እንደሚያሳድግ ካቢኔው እምነቱን ገልጿል
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ካቢኔ ከእስራኤል ጋር የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አፀደቀ
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ምክትል ፕሬዝዳንት ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዱባይ ገዥ መሃመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም መሪነት ፣ የሀገሪቱ ካቢኔ ባለፈው ወር አጋማሽ ከእስራኤል ጋር በአሜሪካ የተፈረመውን የሰላም ስምምነት አፀደቀ፡፡
የኤሚሬቶች መንግስት በ “ትዊተር” የማህበራዊ ድረ ገጽ አድራሻው ላይ እንዳመለከተው በ ሼክ መሀመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም የሚመራው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከእስራኤል ጋር የተፈረመውን የሰላም ስምምነትን እና የተሟላ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን በማፅደቅ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ካቢኔው ስምምነቱን አጽድቆ የፌዴራል አዋጅ ለማውጣት የሕገ-መንግስታዊ አሰራሮች መመሪያ እንዲፈተሸ መርቷል፡፡
ስምምነቱ የቀጣናውን ህዝቦች ፍላጎቶች ለማሟላት ፣ ለሰላምና መረጋጋት መስፈን ጠቃሚ እንደሚሆን ካቢኔው እምነቱን ገልጿል፡፡ በተለይም የኢኮኖሚ ፣ የባህልና የእውቀት ግንኙነቶችን ለማጠናከር መንገድ የሚከፍት በመሆኑ የቀጣናውን ህዝቦች የማያቋርጥ የብልፅግና እና የለውጥ መሻት እንደሚያሳድግም ነው የታመነው፡፡
የእስራኤል መንግስት ካቢኔ እና ክኔሴት (ፓርላማው) በመስከረም ወር አጋማሽ በዋሺንግተን ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ባለፈው ሳምንት ያጸደቀ ሲሆን በፓርላማው አባላት ሰፊ ተቀባይነትም አግኝቷል፡፡