የየመን አማጺያን የእስራኤል መርከብን እንዳገቱ ተገለጸ
እስራኤል በጋዛ የጀመረችውን ጥቃት ካላቆመች ማንኛውንም አይነት ጥቃት ማድረሱን እንደሚቀጥልም አማጺ ቡድኑ ገልጿል
የእስራኤል-ሀማስ/ፍልስጤም ጦርነት ከተጀመረ 45ኛ ቀኑ ላይ ይገኛል
የየመን አማጺያን የእስራኤል መርከብን እንዳገቱ ተገለጽ።
ሃማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ እና ያለተጠበቀ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ከተጀመረ 45ኛ ቀኑን ይዟል።
እስራኤልም ራሴን ለመከላከል በሚል የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ ጋዛ ላይ የጀመረችው ድብደባ ቀጥሏል።
በርካታ ሀገራት እስራኤል የጀመረችውን ጥቃት እንድታቆም ግፊት በማድረግ ላይ ቢሆኑም በጋዛ ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት አሁንም እንደቀጠለ ነው።
ለሀማስ ወግኖ በእስራኤል እና አሜሪካ ላይ ጥቃት በማድረስ ላይ ያለው የየመኑ አማጺ ቡድን ሃውቲንብረትነቱ የእስራኤል የሆነ መርከብ መያዙን አስታውቋል፡፡
አማጺ ቡድኑ በቀይ ባህር ወደብ ላይ ሰራሁት ባለው ወታደራዊ ዘመቻ የእስራኤል መርከብን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ገልጿል፡፡
መርከቡን በየመን ወደብ ዳርቻ ላይ እንዳስቀመጠው የገለጸው ይህ አማጺ ቡድን ከእስራኤል ጋር የተያያዙ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡
የቡድኑ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሪ በሰጡት መግለጫ እስራኤል በፍልስጤማዊያን ላይ የጀመረችውን ጦርነት ካላቆመ ጥቃቱን እንደሚቀጥልበትም ገልጿል፡፡
ማንኛውም ሀገር እና ተቋም ከእስራኤል ጋር እንዳይሰራ ሲል ያስጠነቀቀው የሃውቲ አማጺያን በቀይ ባህር እና አካባቢው እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጽህፈት ቤታቸው በኩል ባወጡት መግለጫ ኢራን ዓለም አቀፉን የባህር ትራንስፖርት እያስተጓጎለች ነው ሲል ከሷል፡፡
ጽህፈት ቤቱ አክሎም ኢራን ለሁቲ አማጺያን ድጋፍ በማድረግ የብሪታንያ ንብረት የሆነ መርከብ በጃፓናዊያን እየተንቀሳቀሰች እያለ ተጠልፋለችም ብሏል፡፡
በዚች መርከብ ላይ አብረው የነበሩ 25 ሰዎች በታጣቂዎቹ ተይዘዋል ያለው ጽህፈት ቤቱ ዩክሬናዊያን፣ ቡልጋሪያ፣ ፊሊፒንስ እና ሜክሲኮ ዜግነት ያላቸው ዜጎች ከመያዛቸው ውጪ አንድም እስራኤላዊያን በመርከቧ ላይ እንዳልተሳፈሩም ገልጿል፡፡