ሩሲያና አረብ ኤምሬትስ ግንኙነታቸውን ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሳደግ ተስማሙ
የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ እና የሩስያ ፕሬዝዳንቶች በሞስኮ ተገናኝተዋል
ዩክሬን እና ሩስያ የእስረኛ ልውውጦችን እንዲያደርጉ አረብ ኤምሬትስ 9 የተሳኩ ሽምግልናዎችን አካሂዳለች
የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢንዛይድ አልናህያን በሩስያ የሚያደርጉትን ይፋዊ የስራ ጉብኝት ጀመሩ፡፡
በትላንትናው እለት አመሻሽ ላይ ሞስኮ የደረሱት ፕሬዝዳንቱ ከሩስያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ኢነርጂ እና ቴክኖሎጂን ጨምሮ በንግድ፣ ኢንቨስተመንት፣ እና ሌሎች ዘርፎች ያላቸውን ግንኙነት ለማሳደግ ተስማምተዋል፡፡
በዛሬው እለት ሁለቱ መሪዎች በነበራቸው ምክክር የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሁለቱ ሀገራ መካል የሚደረገው የንግድ ግንኙነት በሶስት እጥፍ ማደጉን ተናግረዋል፡፡
በዚህም የሀገራቱ ወዳጅነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት እያደገ መምጣቱን ነው ፑቲን ያመላከቱት፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ የእስረኞች ልውውጥን ለማሸማገል ላደረገችው የተሳካ ጥረት ምስጋናቸውን ለፕሬዝዳንቱ አቅርበዋል፡፡
በዚህ አመት ብቻ 9 የእስረኛ ልውውጦችን በተሳካ ሁኔታ ማሸማገል የቻለችው ዩኤኢ በአጠቃላይ በሁለቱም ወገን 2184 እስረኞች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ ችላለች፡፡
በዩክሬን ሩስያ ጦርነት ገለልተኛ አቋም ይዛ የዘለቀችው ዩኤኢ በእስረኞች ልውውጥ በሁለቱ ሀገራት መካከል የገነባቸውን እምነት የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ እና ግጭቱን ለማስቆም ልትጠቀምበት እንደምትፈልግ ትገልጸላች፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢንዛይድ አልናህያን በበኩላቸው በጋዛ እና ዩክሬን የሚደረገው ጦርነት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መቆም እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ሞስኮ እና አቡዳቢ በንግድ ፣ በኢንቨስትመንት እና በሌሎች ቀጠናዊ እና አለምአቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርበው ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳድጉ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከነገ በስቲያ ጥቅምት 12 በካዛን ከተማ በሚጀመረው 16ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይም ለመጀመሪያ ጊዜ ይሳተፋሉ።