የሩሲያ ፕሬዝደንት “ቀንደኛ” ተቀናቃኝ የነበረው ናቫልኒ ባለቤት ለሩሲያ ፕሬዝዳንትነት መወዳዳር እንደምትፈልግ ገለጸች
የ30 አመት እስር ተፈርዶበት በእስርቤት እያለ ህይወቱ ያለፈው ናቫልኒ ባለቤት ዩሊያ ናቫልናያ ኑሮዋን በስደት አድርጋለች
ዩሊያ ናቫልናያ “የፑቲን አስተዳደር በቶሎ እንዲወድቅ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ”ብላለች
የሟቹ የሩሲያ ተቃዋሚ መሪ አሌክሲ ናቫልኒ ባለቤት የሆነችው ዩሊያ ናቫልናያ ለሩሲያ ፕሬዝደንትነት የመወዳደር ፍላጎት እንዳለት ገለጸች፡፡
የሩሲያ መንግስት ቀንደኛ ተቀናቃኝ የነበረው ናቫልኒ ባለቤት ዩሊያ “አንድ ቀን የክሬምሊን ዋና አዛዥ ቭላድሚር ፑቲን በስልጣን ላይ በማይገኙበት ጊዜ ወደ ሩሲያ በመመለስ ለፕሬዚዳንትነት እወዳደራለሁ” ብላለች፡፡
በአክራሪነት ውስጥ ትሳተፋለች የሚል ክስ የቀረበባት ዩሊያ ፕሬዝደንት ፑቲን በስልጣን ላይ እያሉ ወደ ሀገሯ ከተመለሰች ለእስር እንደምትዳረግ ተናግራለች፡፡
በየካቲት ወር በአርክቲክ ውስጥ በሚገኘው የሩሲያ እስር ቤት ናቫልኒ ከሞተ በኋላ፣ የተከፋፈሉትን የሀገሪቱን ተቃዋሚዎችን አንድ ለማድረግ የሚጥር አንድም ጠንካራ የተቃዋሚ መሪ ወደ ፊት አልወጣም፡፡
በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚገኙ የፑቲን መንግስት ተቃዋሚ ቡድኖችም ቢሆኑ በመካከላቸው ከፍተኛ የሀሳብ ግጭት እንዳለ ይነገራል፡፡
ጊዜው ሲደርስ በምርጫ እወዳደራለሁ ያለችው ዩሊያ ናቫልናያ “የፖለቲካ ተቀናቃኜ ቭላድሚር ፑቲን ነው እናም አገዛዙ በተቻለ ፍጥነት እንዲወድቅ ሁሉንም ነገር አደርጋለሁ” ስትል ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቃለ መጠይቅ ተናግራለች፡፡
ናቫልኒ በበሽታ እንደሞተ በሩሲያ መንግስት ቢነገርም በፑቲን ተመርዞ እንደተገደለ የምታምነው ዩሊያ “የሩስያ መንግስት ተቃዋሚዎቹን ዝም ለማስባል የማያደርገው ነገር የለም” ስትል በተደጋጋሚ ተደምጣለች፡፡
ክሪምሊን በበኩሉ ሟቹ የፑቲን ብርቱ ተቀናቃኝ ናቫልኒ እና አጋሮቹ “ከምዕራባውያን ጋር በማበር ሀገሪቱን ለማተራመስ የሚሰራ አክራሪ ቡድን አባላት እንደሆኑ” ይገልጻቸዋል፡፡
ናቫልኒ “የፑቲንን መንግስት በሌቦችእና በሰላዮች የሚተዳደር ለገንዘብ ብቻ የሚያስቡ ወንጀለኛ መንግስት ነው” ሲል በተደጋጋሚ የሰላ ትችት ይሰነዝራል፡፡
በተጨማሪም ፑቲን መሬት አንቀጥቃጭ አብዮት እና ተቃውሞ በቅርቡ እንደሚያጋጥማቸው ይተነብይ ነበር፡፡
ዩሊያ ናቫልኒያ በአሁኑ ወቅት ከሁለት ልጆቿ ጋር በለንደን እየኖረች ሲሆን ለእርሷ እና ለቤተሰቧ ደህንነት ሲባል ወደ ሞስኮ የመመለስ ሀሳብ እንደሌላት ተናግራ ነገር ግን ትግሏን ከሀገር ውጭ ሆናም እንደምትቀጥል ገልጻለች፡፡