የሱዳን ጦር ከፍተኛ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር አዛዥ ከድቶ እንደተቀላቀለው ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ አደረገ
የሱዳን ጦር የተቀናቃኙ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር አዛዥ የተወሰኑ ወታደሮችን አስከትሎ መክዳቱን በትናንትናው እለት አስታውቋል
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች አዛዡ የከዳው በስምምነት መሆኑን እና ከእሱ ጋር በከዱ ወታደሮች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጉን ገልጿል
የሱዳን ጦር ከፍተኛ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር አዛዥ ከድቶ እንደተቀላቀለው ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ አደረገ።
የሱዳን ጦር የተቀናቃኙ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር አዛዥ የተወሰኑ ወታደሮችን አስከትሎ መክዳቱን በትናንትናው እለት አስታውቋል። ይህ በከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ የተፈጸመው የመክዳት እርምጃ ሁለቱ ወገኖች ከ18 በላይ ወራት ያስቆጠረውን ጦርነት ከጀመሩ ወዲህ የመጀመሪያው ነው።
የሱዳን ጦር ደጋፊዎች የቀድሞ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች የኢል ገዚራ ግዛት ከፍተኛ አዛዥ አቡአግላ ኬይካል ከከዳ በኋላ የሚያሳይ ፎቶ በኦንላይን ለቀዋል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር ዘግየት ብሎ ባወጣው መግለጫ ኬይካል የከዳው ስምምነት ውስጥ ከገባ በኋላ መሆኑን እና ከእሱ ጋር በከዱ ወታደሮች ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርጓል የሚል ክስ አቅርቧል።
በቅርቡ በካርቱም ከተማ የተወሰኑ ክፍሎች በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ላይ የበላይነት መያዙን የገለጸው ጦሩ፣ ኬይካል ይህን የወሰነው በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ "አውዳሚ አጀንዳ" ምክንያት ነው ብሏል።
ኬይካል በዚህ ጉዳይ አስተያየት አለመስጠቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በአለም አስከፊ የሰብአዊ ቀውስ ባስከተለው ጦርነት አብዛኛውን የሱዳን ክፍል መቆጣጠር ችሏል። ጦርነቱ 10 ሚሊዮን ሰዎች እንዲፈናቀሉ፣ አብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል ለድርቅ ውይም ለረሀብ እንዲጋለጥ እና የውጭ ኃይሎች ለሁለቱም ወገን ድጋፍ እንዲያርጉ ጋብዟል።
በጀነራል አል ቡርሃን በሚመራው የሱዳን ጦር እና በጀነራል መሀመድ ሀምዳን ደጋሎ ወይም ሄሜቲ በሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል ጦርነት የቀሰቀሰው በ2023 ነበር።
ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ሀገሪቱን ለረጅም ጊዜ የመሩት ኡመር ሀሰን አል በሽር በህዝባዊ አመጽ ከስልጣን ከተወገዱ ከሁለት አመት በኋላ በ2021 በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ላይ መፈንቅለ መንግስት አድርገው ስልጣን ተጋርተው ነበር።