እስራኤል በተፈናቃዮች መጠለያ ጣብያ ላይ በፈጸመችው ጥቃት ከ70 በላይ ሰዎች ተገደሉ
የተመድ መረጃ እንደሚያሳየው 99 በመቶ የጋዛ ነዋሪ ከቀየው ተፈናቅሎ በመጠለያ ጣብያዎች ውስጥ ይገኛል
እስራኤል በበኩሏ ስፍራው 20 የሀማስ ታጣቂዎች ጥቃት ለመፈጸም ሲዘጋጁ የነበሩበት ነው ብላለች
እስራኤል በጋዛ ተፈናቃዮች ተጠልለው በሚገኙበት ትምህርት ቤት ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ከ70 ባላይ ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡
ጥቃት በተፈጸመበት ትምህርት ቤት በርካታ ተፈናቃዮች የሚገኙበት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ተነግሯል፡፡
ሟቾችን በተመለከተ ቢቢሲ እና ሮይተርስ 70 መሆናቸውን ሲዘግቡ አጃንስ ፍራንስ ፕረስ በበኩሉ ቁጥሩ ወደ 90 እንደሚጠጋ ዘግቧል፡፡
ጥቃት የተፈጸመበት አል ታባ ትምህርት ቤት እስከ አንድ ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮች ተጠልለው የሚገኙበት ሲሆን የአየር ጥቃቱ በቅጥሩ ውስጥ በሚገኝ መስጂድ የንጋት ጸሎት እያደረጉ በሚገኙ ተፈናቃዮች ላይ መፈጸሙ ተነግሯል፡፡
የእስራኤል መከላከያ ሀይል ቃል አቀባይ ጥቃቱን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ ትምህርት ቤቱ ሀማስ ለወታደራዊ ዘመቻዎች የሚጠቀምበት እና በስፍራውም 20 የሚደርሱ የቡድኑ ታጣቂዎች ይገኙ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡
ቃል አቀባዩ ሌተናል ኮለኔል ናዳቭ ሾሻኒ እንደተናገሩት ተፈናቃዮችን ከለላ በማድረግ ከፍተኛ የሀማስ ወታደራዊ አመራር በስፍራው ዘመቻ ለመምራት ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበር የተረጋገጠ መረጃ ደርሶናል ብለዋል፡፡
በጋዛ የጤና ባለስልጣናት የተነገረው የሟቾች ቁጥር የተጋነነ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ ጥቃቱ ትክክለኛውን ኢላማ ታሳቢ አድርጎ የተፈጸመ ነው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
እስራኤል በላፉት ሳምንታት በጋዛ ካን የኑስ እና በተለያዩ ስፍራዎች በሰፊው እያደረገችው ባለው ጥቃት የተለያዩ የተፈናቃይ መጠለያዎችን ኢለማ አድርጋ ጥቃት ፈጽማለች፡፡
እንደተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ከሆነ በጋዛ ከሚገኙ 564 የትምህርት ቤት ህንጻዎች ውስጥ 477 በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የጥቃት ሰለባ ሁነዋል፡፡
አሜሪካ፣ ግብጽ እና ኳታር በሀማስ እና እስራኤል መካከል አስቸኳይ ድርድር እንዲደረግ ጠየቁ
ከ ሁለት ሚለየን በላይ ዜጎች በሚኖሩበት ጋዛ 10 ወራትን ባስቆጠረው ጦርነት 99 በመቶ ነዋሪዎች ከቀያቸው ተፋንቀለው በመጠለያ ጣብያዎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡
በጦርነቱ ጉዳት ከሚደርሰባቸው ዜጎች በተጨማሪም በምግብ እና በህክምና እጥረት የዜጎች ህይወት እያለፈ እንደሚገኝ ተመድ በማሳሰብ ላይ ነው፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ በመጪው ሳምንት ሀሙስ እስራኤል እና ሀማስ በአስቸኳይ ለድርድር እንዲቀመጡ አሜሪካ ግብጽ እና ኳታር ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡