አሜሪካ፣ ግብጽ እና ኳታር በሀማስ እና እስራኤል መካከል አስቸኳይ ድርድር እንዲደረግ ጠየቁ
ሀገራቱ በመጪው ሳምንት ሀሙስ ድርድሩ እንዲካሄድ ነው ጥሪ ያደረጉት
በመካለኛው ምስራቅ ቀጠና እየተባባሰ ለሚገኘው የጦርነት ስጋት የጋዛው ጦርነት መቆም ወሳኝ መሆኑን በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል
አሜሪካ፣ ግብጽ እና ኳታር እስራኤል እና ሀማስ በአስቸኳይ ለድርድር እንዲቀመጡ ጠየቁ ፡፡
ተዋጊዎቹን ለማደራድር ጥረት እያደረጉ የሚገኙት ሶስቱ ሀገራት በቀጠናው የሚገኝው ወቅታዊ ሁኔታ ወደለየት ጦርነት ከማምራቱ በፊት አቁመውት የነበረውን ድርድር እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
በኳታር ዶሀ አልያም በግብጽ ካይሮ ይደረጋል በተባለው ድርድር የመደራደርያ አጀንዳዎች ተዘጋጅተው መጠናቀቃቸውን በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ድርድሩን ለማካሄድ ሁለቱ ተፋላሚዎች የሚያቀርቡትን ቅድመ ሁኔታ እና ምክንያት በመተው ታጋቾች በሚለቀቁበት እና የተኩስ አቁም በሚደረግበት ሁኔታ ላይ በፍጥነት ተገናኝተው እንዲመክሩ ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አደራዳሪዎቹ ሀማስ እና እስራኤል ከስምምነት ባልደረሱባቸው ነጥቦች ላይ የሚቀራርብ አዲስ የማግባብያ ፕሮፖዛል በድርድሩ ላይ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ እያየለ የመጣውን የቀጠናዊ ጦርነት ስጋት ለመቀልበስ የጋዛው ጦርነት መቆም ወሳኝ ነው ያሉት አደራዳሪዎቹ ተፋላሚዎቹ ውጥረቱን ከሚያባብሱ ሁኔታዎች በመታቀብ ወደ ሰላም አማራጮች ያማትሩ ዘንድ አሳስበዋል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለድርድር ጥሪው በሰጡት ምላሽ የእስራኤል ተደራዳሪዎች በተባለው ቀን በድርድር ስፍራው እንደሚገኙ ቃል የገቡ ሲሆን በቅርቡ የፖለቲካ ቢሮ መሪው የተገደለበት ሀማስ እስካሁን በይፋ ምላሽ አልሰጠም፡፡
ሮይተርስ ያነጋገራቸው የአደራደሪ ቡድን አባል እንዳሉት የእስማኤል ሀኒየህን ግድያ ተከትሎ በአካባቢው ያለው ውጥረት በከፈተኛ ሁኔታ በመጨመሩ በሁለቱ ወገኖች መካከል በመጪው ሳምንት የስምምነት ፊርማ ይፈራረማሉ ማለት ባይቻልም ለድርድር መቀመጣቸው ግጭቱን ለመቋጨት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡
ሀማስ እና እስራኤል ለድርድር ሳይቀመጡ በፊት ከሂዝቦላ እና ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት የሚሰነዘር ከሆነ ግን ሁኔታዎችን ሊያወሳስብ ይችላል ነው ያሉት፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢራን አምባሳደር በበኩላቸው በጋዛው ጦርነት ሁለት ነገሮች ጎን ለጎን እንዲፈጸሙ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
እነርሱም የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እና እስራኤል ጋዛን ለቃ በአፋጣኝ ለቃ እንድትወጣ ነው፡፡
ሂዝቦላ በበኩሉ ቴልአቪቭ በሀማስ ላይ ያወጀችውን ጦርነት እስካላቆመች ድረስ የሚያደርሰውን ጥቃት እንደሚቀጥል ዝቷል፡፡