እስራኤል በጋዛ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በፈጸመችው ጥቃት 70 ሰዎች ተገደሉ
የቴል አቪቭ አውሮፕላኖች መንገዶችን ጭምር በመደብደብ አምቡላንሶች እንዳይንቀሳቀሱ አድርገዋል ብሏል የፍልስጤም ቀይ መስቀል
ግብጽ በሶስት ምዕራፍ የሚተገበር ረቂቅ የተኩስ አቁም ስምምነት ማዘጋጀቷ ተገልጿል
እስራኤል በአል ማግሃዚ የስደተኞች ጣቢያ ላይ በፈጸመችው የአየር ድብደባ በጥቂቱ 70 ሰዎች መገደላቸው ተነገረ።
በ11 ሳምንታት የእስራኤል ዘመቻ ከባድ ነው በተባለው ጥቃት የሟቾቹ ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችልም የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የእስራኤል አውሮፕላኖች መንገዶችን ጭምር በመደብደባቸው አንቡላንሶች ለመንቀሳቀስ መቸገራቸውን የፍልስጤም ቀይ መስቀል ገልጿል።
“ከማዕከላዊ ጋዛ ለቀቁ ብለውን ብንወጣም ከጥቃት አልዳንም፤ ሴት ልጄን፣ ባሏንና ልጃቸውን በሙሉ አጥቻለሁ፤ ንጹሃንን ኢላማ ያደረጉ ግድያዎች ቀጥለዋል” ብለዋል አስተያየታቸውን ለቢቢሲ ያጋሩ አንድ አባት።
እስራኤል በበኩሏ የንጹሃንን ጉዳት ለመቀነስ ጥረት አድርጌያለው፤ በአ፡ ማግሃዚ ካምፕ ጥቃት ዙሪያ ምርመራ ጀምሬያለው ብላለች።
ሃማስ ባይቀበለውም የስደተኞች ጣቢያውን እንደ ሰብአዊ ጋሻ ተጠቅሞበታል የሚል ወቀሳ ከቴል አቪቭ በኩል ይቀርብበታል።
በአል ማግሃዚ የስደተኞች ጣቢያ ላይ ከባድ ጥቃት የተፈጸመው ግብጽ በሶስት ምዕራፍ የተከፋፈለ ረቂቅ የተኩስ አቁም ስምምነት ይፋ ባደረገች ማግስት ነው ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ተኩስ አቁም ሃማስ ሁሉንም ሲቪል ታጋቾች ይለቃል፤ እስራኤልም የተወሰኑ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ትፈታለች ይላል ረቂቁ። ይህም ከሰባት እስከ 10 ቀናት ይወስዳል ተብሎ ይጠበቃል።
ለሰባት ቀናት በሚቆየው ሁለተኛው ምዕራፍ ተኩስ አቁም ደግሞ ሃማስ ሁሉንም ሴት እስራኤላውያን ወታደሮች እንዲለቅና በምትኩም እስራኤል በርካታ ፍልስጤማውያን እስረኞችን እንድትለቅ ይደረጋል።
ለአንድ ወር በሚዘልቀው ሶስተኛው ምዕራፍ ደግሞ ሃማስ ታጋቾችን ሙሉ በሙሉ እንዲለቅ እና እስራኤልም ከጋዛ እንድትወጣ፤ የአየር ድብደባዋም እንድታቆም ይጠይቃል የካይሮ ረቂቅ ስምምነት።
መሪውን ኢስማኤል ሃኒየህ ወደ ካይሮ የላከው ሃማስ ረቂቅ የስምምነት ሰነዱን እያጤነው መሆኑን የገለጸ ሲሆን፥ በእስራኤል በኩልም ተቀባይነት ሊያገኝ እንደሚችል የእስራኤልና የአረብ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው።