የጋዛ ጦርነት ለተጨማሪ 7 ወራት ሊራዘም እንደሚችል ተነገረ
የእስራኤል ጦር በራፋህ የሚያደርገው ዘመቻ የመጨረሻው የጦርነቱ ምዕራፍ እንደሚሆን ተናግሮ ነበር
የተኩስ አቁም ስምምነት እና የጋዛ ቀጣይ አስተዳደራዊ ሁኔታ በእስራኤል መንግስት መካከል ክፍፍልን ፈጥሯል
እስራኤል በጋዛ እያደረገቸው ያለው ጦርነት እስከ ፈረንጆቹ አመት መጨረሻ ሊቀጥል እንደሚችል የእስራኤል ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ዛኪ ሃኒግቢ ተናግረዋል፡፡
“የአመቱ 6ተኛ ወር ላይ እንገኛለን፤ በእስካሁኑ ጦርነት የሀማስን መሰረታዊ ወታደራዊ አቅሞችን ማዳከም ብንችልም ቡድኑ አሁንም ሊያንሰራራ እንደሚችል ስጋት አለ” ብለዋል አማካሪው፡፡
የእስራኤል የጦር ካቢኔ አባላት አሁንም በራፋ የሚደረገው ውግያ መቀጠል እንዳለበት ፣ሃማስን ማጥፋት ታጋቾችን ከማስመለስ በላይ ጠቃሚ ነው ብለው ያምናሉ፡፡
ራፋህ የመጨረሻው የጋዛ ጦርነት መዳረሻ ነው ያለው የእስራኤል ጦር የሃማስን ታጣቂዎች አወድሜበታለሁ ባለው በሰሜናዊ ጋዛ ሲንቀሳቀስ ታይቷል፡፡ እንደ ሲኤንኤን ዘገባ ከሆነ በሰሜን ጋዛ እየታየ ያለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ጦርነቱ ሊራዘም እንደሚችል አመላካች ነው፡፡
በራፋህ በቅርቡ በተፈናቃዮች መጠለያ ባደረሰቸው የአየር ጥቃት አለምአቀፋዊ ውግዘት እና ተጽእኖ የበረታባት ቴልአቪቭ በአሜሪካ በቀረበው የተኩስ አቁም ጥያቄ ላይ እየመከረች ነው፡
ኔታንያሁ የተኩስ አቁም ድርድሩን በመቀበል እና መንግስታቸውን ከመበተን ለመከላከል በሚሉ በሁለት ሀሳቦች ተወጥረው ይገኛሉ፡፡
አሜሪካ ያቀረበችውን የተኩስ አቁም የምትቀበል ከሆነ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ፓርቲ ጋር ጥምር መንግስት የመሰረቱ ፓርቲዎች መንግስት እንዲፈርስ ለፓርላማው ጥያቄ እናቀርባለን በሚል እየዛቱ ነው፡፡
ሀማስ ሙሉ ለሙሉ ሳይደመሰስ የጦርነት ማቆምም ሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት መፈጸም የለበትም የሚሉት ፓርቲዎች ለኔታንያሁ አስተዳደደር መዝለቅ ስጋትን ደቅነዋል፡፡
በፍልስጤም እና በእስራኤል በኩል እንዲኖር በመፍትሄነት እየቀረበ የሚገኝው የሁለት መንግስት አስተዳደር እና የጋዛ አስተዳዳራዊ ሁኔታ ከተኩስ አቁም ስምምነቱ በተጨማሪ የልዩነት አጀንዳዎች ሆነው ይገኛሉ፡፡
ኔታንያሁ የአሜሪካን የተኩስ አቁም ጥያቄ የሚቀበሉ ከሆነ መንግስታቸው ሊበተን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ እያየለ የመጣው አለምአቀፋዊ ውግዘት እና አሁንም በሀማስ እጅ የሚገኙ እስራኤላዊያን ታጋቾች ጉዳይም በጥያቄ ውስጥ ነው፡
በጋዛ የሚደረገው ግጭት በቶሎ መፍትሄ ካልተበጀለት በንጹሀን ላይ እየደረሰ ያለው ሰብአዊ ጉዳት ከዚህ ሊከፋ ይችላል ያለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረስ ጠይቋል፡፡
እንደ ተመድ መረጃ ከሆነ እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ ራፋ ጥቃት ከጀመረች ጀምሮ ወደ ጋዛ የሚገባው ሰብአዊ ድጋፍ በሁለት ሶስተኛ ወይም 67 በመቶ ቀንሷል፡፡