አሜሪካ ለእስራኤል ተጨማሪ የጦር አውሮፕላኖችና ቦምቦች እንዲላኩ አዘዘች
የቴል አቪቭ ልኡክ የፊታችን ሰኞ በዋሽንግተን በራፋህ ጦርነት እቅድ ዙሪያ ገለጻ ያደርጋልም ተብሏል
የባይደን አስተዳደር በጋዛው ጦርነት ስጋቱን እየገለጸ ንጹሃን የሚያልቁባቸውን የጦር መሳሪያዎች ማቅረቡን ቀጥሏል
አሜሪካ ለእስራኤል ተጨማሪ የጦር አውሮፕላኖች እና ቦምቦችን ለመላክ መስማማቷ ተነገረ።
ዋሽንግተን ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ የጦር አውሮፕላኖች፣ 1 ሺህ 800 ኤምኬ84 እና 500 ኤምኬ82 ቦምቦችን ወደ ቴል አቪቭ እንዲላኩ ማዘዟን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ሁለት የአሜሪካ ባለስልጣናትን ጠቅሶ ዋሽንግተን ፖስት አስነብቧል።
የባይደን አስተዳደር የጦር መሳሪያ ሽያጩን ያጸደቀው እስራኤል በጋዛ እየፈጸመችው ያለው የቦምብ ድብደባ ከፍተኛ አለማቀፍ ውግዘት እያስተናገደ ባለበት ወቅት ነው።
አረብ አሜሪካውያን እና የዴሞክራት ፓርቲ አባላት ጭምር አሜሪካ ለእስራኤል የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንዳታደርግ እየጠየቁ ቢሆንም ዋሽንግተን ተጨማሪ የጦር አውሮፕላኖች እና ቦምቦችን ለመላክ ወስናለች።
ፕሬዝዳንት ባይደን በርካታ አረብ አሜሪካውያን በጋዛው ጦርነት የሚሰማቸውን ህመም እጋራለሁ ቢሉም ለእስራኤል የሚደረገው ድጋፍ ከኔታንያሁ ጋር በገጠመው ልዩነት ምክንያት አይቋረጥም ማለታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ዋይትሃውስም ሆነ በአሜሪካ የእስራኤል ኤምባሲ ስለአዲሱ የጦር መሳሪያ ድጋፍ መረጃ ለመስጠት አልፈለገም።
ይሁን እንጂ በአሜሪካ ለቀናት ቆይታ ያደረጉት የእስራኤሉ የመከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት ከአሜሪካ አቻቸው ሊዩድ ኦስቲን ጋር ሲመክሩ ዋነኛ አጀንዳቸው የጦር መሳሪያ ጉዳይ ነበር ተብሏል።
ሚኒስትሩ ሀገራቱ የገቡበት ውጥረት እንደሚረግብና የአሜሪካ ድጋፍ እስራኤል በቀጠናው ጠንካራ ወታደራዊ አቅም እንዲኖራት ማስቻሉንም መናገራቸው ይታወሳል።
አዲሱ ስምምነት ለእስራኤል በአመት ከ3 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር በላይ ወታደራዊ ድጋፍ የምታደርገው አሜሪካ በጋዛው ጦርነት አጋሯን የተቃወመች ትምሰል እንጂ ጦርነቱ ይቀጥል በሚለው ዙሪያ ከኔታንያሁ የተለየ አቋም እንደሌላት ማሳያ ተደርጎ ቀርቧል።
በጸጥታው ምክርቤት አስገዳጅ የተኩስ አቁም እንዲደረግ በተላለፈው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ድምጸ ተአቅቦን መምረጧ የሀገራቱን ግንኙነት እንደረበሸ በሚዲያዎች የሚተላለፈውም የይስሙላ ነው ይላሉ ተንታኞች።
እስራኤል በአሜሪካ ውሳኔ ተበሳጭቻለሁ በሚል ወደ ዋሽንግተን ሊያመራ የነበረ የልኡካን ቡድኗን ጉዞ መሰረዟ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ የጦር መሳሪያ ድጋፉ በተሰማበት እለት ልኡኩ የፊታችን ሰኞ በዋሽንግተን ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝቶ በራፋህ ጦርነት እቅድ ዙሪያ ይመክራል ተብሏል።