የግብጽ ደህንነቶች የውጭ ዜጎች ለማስወጣትና እርዳታ እንዲገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል
እስራኤል በደቡብ ጋዛ ምንም አይነት የተኩስ አቁም ስምምነት አልተተገበረም ብላለች።
ምንም እንኳን የግብጽ የደህንነት ምንጮች የውጭ ዜጎች ከፍልስጤም ለቀው እንዲወጡ እና እርዳታ እንዲገባ ለማድረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል ቢሉም እስራኤል ተኩስ ለማቆም እቅድ የለኝም ብላለች።
በጋዛ ላይ የሚካሄደው የቦምብ ድብደባ ሌሊቱን ሙሉ የቀጠለ ሲሆን፤ ነዋሪዎች ዘጠኝ ቀናት በዘለቀው ግጭት ከፍተኛው ድብደባ መሆኑን ጠቁመዋል።
ጋዛ ሰብዓዊ ቀውስ የገጠማት ሲሆን፤ ሁለት የግብጽ የደህንነት ምንጮች እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ ላይ የምታደርገውን የቦምብ ድብደባ ለማቆም መስማማቷን ገልጸዋል።
ምንጮቹ በግብጽ ቁጥጥር ስር ባለው የራፋህ ድንበር ማቋረጫ የውጭ ሀገር ፓስፖርት የያዙ ሰዎችን ለማስወጣት ይከፈታል ብለዋል።
ነገር ግን የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፤ "የውጭ ዜጎችን ለማስወጣት በአሁኑ ጊዜ በጋዛ ምንም አይነት ስምምነት እና ሰብዓዊ እርዳታ የለም" ብሏል።
ከሳምንት በፊት በእስራኤል ጥቃት የሰነዘረው የሀማስ ባለስልጣናት ተደረገ ስለተባለው የተኩስ አቁም ስምምነት አላረጋገጡም።
ለጋዛ እርዳታ ለማድረስ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
እስራኤል ሀማስን "ከምድረ ገጽ" ለማጥፋት ለመሬት ወረራ እየተዘጋጀች ነው።