ሃማስም ሮኬተ መተኮሱን የቀጠለ ሲሆን፤ የጋዛ ነዋሪዎቹም ቤታቸውን ለቀው እየሸሹ ነው
ሃማስ ባሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ በእስራኤል ላይ ያለተጠበቀ እና ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘረሩን ተከትሎ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል የተጀመረው እንደቀጠለ ነው።
እስራኤል አዳሩን ጋዛ ከተማን በአየር ስትደበድብ ያደረች ሲሆን፤ በደቡባዊዋ ካን ዮኒስ በኩል ጦሯን በማስገባት ወረራ አድርጋለች።
የሃማስ ተዋጊዎች ሌሊቱን ወደ እስራኤል ቴል አቪቭ ከተማ ሮኬቶችን ተኩሰዋል።
የእስራኤል ጦር በጋዛ ላይ "በአየር፣ በባህር እና በየብስ በተቀናጁ ጥቃቶች" ለማስፋፋት ያለውን ዝግጁነት ገልጿል።
የእስራኤል ጦር በጋዛ እያካሄደ ባለው የአየር ጥቃት የሀማስን የአየር ኃይል አዛዥ ሙራድ አቡ ሙራድን መግደሉን አስታውቋል።
እስራኤል ከትናንት በስትያ 1.1 ሚሊዮን የሚሆኑ የሰሜን ጋዛ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን እንዲለቁ ባስጠነቀቀችው መሰረት፣ ነዋሪዎች እየተሰደዱ ይገኛሉ።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር በታጣቂ ቡድኑ ታግተው የተወሰዱ ሰዎችን ለማስለቀቅ በጋዛ የመሬት ጥቃት እያካሄደ መሆኑን ገልጿል።
አሜሪካ በበኩሏ ኢራን እና ሊባኖስ ሄዝቦላን ለመከላከል ሁለተኛውን የአውሮፕላን ተሸካሚ ግዙፍ የጦር መርከብ ወደ ምስራቃዊ ሜዲትራኒያን ማንቀሳቀሷተናግሯል።
ቀጠናዊ ውጥሩም እያደገ የመጣ ሲሆን፤ ኢራን እስራኤል በጋዛ የጦር ወንጀሏን ከቀጠለች መቋቋም የማትችለው የተቃውሞ ማእበል ያጋጥማታል ስትል አስጠንቅቃለች።
እስራኤል በሶሪያ አሌፖ በፈተመችው የአየር ድብደባም በአሌፖ ከተማ የሚገኘውን አየር ማረፊያ ከአገልግሎት ውጪ እንዳደረገው የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሟቾች ቁጥር
በሃማስ ጥቃት እና በእስራኤል የአየር ድብደባ ከሁለቱም ወገኖች የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ3 ሺህ 500 ማለፉ ተነግሯል።
የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ 2 ሺህ 215 ሰዎች በጋዛ በደረሰው የአየር ጥቃት ተገድለዋል። 8714 በላይ የሚሆኑት ደግሞ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ሀማስ በሰነዘረው ጥቃት 1300 ሰዎች መገደላቸውንና ከ3 ሸህ በላይ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን እስራኤል ገልጻለች።