የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር የሀማስ ታጣቂዎችን ለመዋጋት እና በታጣቂ ቡድኑ ታግተው የተወሰዱ ሰዎችን ለማስለቀቅ በጋዛ የመሬት ጥቃት እያካሄደ መሆኑን ገልጿል
የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶች በማዝነብ እና በታጣቂዎቹ በመታገዝ በእስራኤል በ50 አመታት ውስጥ ከባድ የተባለ ጥቃት አድርሷል።
ሀማስ የእስራኤልን ድንበር በመጣስ ጥቃት ከሰነዘረ አንድ ሳምንት አስቆጥሯል።
በጥቃቱ የተቆጣችው እስራኤል ጦርነት በማወጅ የሀማስ ይዞታ በሆነችው ጋዛ ላይ መጠነሰፋ ጥቃት አድርሳለች፣ በማድረስ ላይም ትገኛለች።
ሀማስን ከምደረ ገጹ አጠፋለሁ ያለችው እስራኤል ከትናንት በስትያ 1.1 ሚሊዮን የሚሆኑ የሰሜን ጋዛ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን እንዲለቁ ባስጠነቀቀችው መሰረት፣ ነዋሪዎች እየተሰደዱ ይገኛሉ።
እስራኤል በተከበበችው ጋዛ የምታደርገው የአየር ድብደባ ሲቀጥል፣ የሰማን ጋዛ ነዋሪዎች በመኪና፣ በጭነት መኪና እና በአህያ ጓዛቸውን ጭነው ቀያቸውን ለቀው እየተሰደዱ መሆኑን ስካይ ኒውስ ዘግቧል።
ሀማስ በተሽከርካሪ ሲሄዱ የነበሩ በአብዛኛው ሰቶች እና ህጻናትን ጨምሮ በአየር ድብደባው 70 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።
ተመድ እና የእርዳታ ድርጅቶች የሰብአዊ ቀውስ እንደሚፈጠር በመግለጽ እስራኤል እቅዷን እንድትቀይር ቢጠይቁም፣ እስራኤል በውሳኔዋ ላይ ደግማ ማሰብ አልፈለገችም።
እስራኤል አሁን ያስቀመጠችውን የ24 ሰአት ገደብ በማራዘም ሰዎች በሁለት አቅጣጫ ወደ ደቡብ ጋዛ እንዲሄዱ እያደረገች ነው።
የእስራኤል በመሬት ጥቃት መጀመር
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር የሀማስ ታጣቂዎችን ለመዋጋት እና በታጣቂ ቡድኑ ታግተው የተወሰዱ ሰዎችን ለማስለቀቅ በጋዛ የመሬት ጥቃት እያካሄደ መሆኑን ገልጿል።
እስራኤል ወታደሮቿን ወደ ጋዛ ማስገባቿን ስትገልጽ ይህ የመጀመሪያዋ ነው።
የእስራኤል ሚዲያዎች እንደዘገቡት ከሆነ የእስራኤል መከላከያ ባደረገው አሰሳ የጠፉ ሰዎች አካል መገኘቱን ዘግበዋል።
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው ከሊባኖስ ዘልቀው ለመግባት የሞከሩ ታጣቂዎችም ተገድለዋል።
የማቾች ቁጥር
የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ 1900 ሰዎች በጋዛ በደረሰው የአየር ጥቃት ተገድለዋል። 7600 በላይ የሚሆኑት ደግሞ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ሀማስ በሰነዘረው ጥቃት 1300 ሰዎች መገደላቸው እስራኤል ገልጻለች።
ሀማስ ግጭቱን በንግግር ለመፍታት ፍላጉትን ቢገልጽም እስራኤል ግን ጋዛን በመክበብ እና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጦር በማሰማራት ማጥቃቷን ቀጥላለች።
በተመሳሳይ በተመድ የፍልስጤም ተወካይ በእስራኤል እየተፈጸመ ነው ያሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ተመድ እንዲያስቆም ጠይቀዋል።