ለፕሬዝዳንት ኤርዶሀን በቱርክ ታሪክ ከፍተኛ ህዝብ የታደመው የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ
የቱርክ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከአንድ ሳምንት በኋላ እንደሚካሄድ ይጠበቃል
ለፕሬዘዳንት ኤርዶሀን ድጋፍ በሚል እስከ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ህዝብ የተሳተፈበት የድጋፍ ሰልፍ በኢስታምቡል ተካሂዷል
የቱርክ ፕሬዝዳንታዊ እና ህግ አውጪዎች ምክር ቤት ምርጫ ሊካሄድ አንድ ሳምንት ቀርቶታል።
የቱርካዊያንን እና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት የሳበው ይህ ምርጫ ፕሬዝዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶሀን ለተጨማሪ አምስት ዓመታት በስልጣን ላይ ሊቆዩ አልያም የስልጣን ዘመናቸው እዚህ ላይ እንዲያበቃ ሊያደርግ ይችላል ተብሏል።
በቱርክ የኢኮኖሚ ዋና ከተማ በሆነችው ኢስታምቡል እስከ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብ ለሰላማዊ ሰልፍ ወደ አደባባይ ወጥተዋል።
ለፕሬዝዳንት ኤርዶሀን እና ፓርቲያቸው ድጋፍ ለማድረግ የተሰናዳው ይህ ሰልፍ በታሪክ ከፍተኛ ህዝብ የታደመው የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሆነ አናዶሉ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ኤርዶሀን ለሰልፉ ታዳሚዎች ባደረጉት ንግግር መንግስታቸው ባለፉት 21 ዓመታት 10 ነጥብ 5 ሚሊዮን መኖሪያ ቤቶችን ገንብቷል ብለዋል።
እንዲሁም ፓርቲያቸው በምርጫ ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ የቱርካዊያንን የገቢ ምንጭ ከሶስት እጥፍ እና ከዛ በላይ እንዲጨምር ማድረጉንም ፕሬዝዳንቱ አክለዋል።
የቱርክ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፍ ተጽዕኖን አሳድገናል ያሉት ፕሬዝዳንት ኤርዶሀን በወታደራዊ ቴክኖሎጂ ዙሪያም ስኬታማ ስራዎችን አከናውነናል ብለዋል።
በቀጣዩ ምርጫም እሳቸው እና ፓርቲያቸው ካሸነፈ በጥቁር ባህር አካባቢ የተገኘው የቢሊዮን ዶላርሮች ዋጋ ያለውን ነዳጅ ለዓለም አቀፍ ገበያ እንዲቀርብ አደርጋለሁ ሲሉ ቃል ገብተዋል።
እንዲሁም ቱርክ የዓለም አቀፍ ባህር ትራንስፖርት ማዕከል የሚያደርጋትን በኢስታምቡል መርከቦች መተላለፊያ መስመርን እንገነባለን ሲሉ ለቱርካዊያን ቃል ገብተዋል።
የቱርክ ፕሬዝዳንታዊ እና ህግ አውጪ ምርጫ የፊታችን እሁድ የሚካሄድ ሲሆን ከፍተኛ ፉክክር እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
ከማል ኪሊስዳሮግሉ፣ ሙሀሪም ኢንስ እና ሲናን ኦጋን በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ላይ እጩ ሆነው የቀረቡ ሲሆን ቱርክን ላለፉት 9 ዓመታት የመሩት ፕሬዝዳንት ኤርዶሀን ዋነኛ ተፎካካሪዎች እንደሆኑ ተገልጿል።
የቀድሞው የኢስታምቡል ከንቲባ እና የአሁኑ የቱርክ ፕሬዝዳንት ኤርዶሀን ቱርክን ከፈረንጆቹ 2014 ጀምሮ በፕሬዝዳንትነት እየመሩ ይገኛሉ።