“ጥቂት የፖሊስ ኃይሎችን የመደብን ቢሆንም ታጣቂዎቹ ሲመጡ ሸሽተው መጥፋታቸው አሳዝኖናል”- አሻድሊ ሃሰን
በቸልተኝነት ጥቃቱ እንዲፈጸም ባደረጉ የሥራ ኃላፊዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም ተጠቁሟል
ተጎጂዎችን ማቋቋምና በወንጀሉ የተሳተፉትን በቁጥጥር ሥር ማዋል ቀጣይ ተግባራት ናቸው ተብሏል
“ጥቂት የፖሊስ ኃይሎችን የመደብን ቢሆንም ታጣቂዎቹ ሲመጡ ሸሽተው መጥፋታቸው አሳዝኖናል”- አሻድሊ ሃሰን
ከሰሞኑ የደረሰው ጥቃት ኢ-ሰብዓዊ እና መደገም የሌለበት እንደሆነ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሠ መሥተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ፡፡
በጥቃቱ ማዘናቸውን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ክልሉ ከጥቃቱ በፊት በደረሰው መረጃ በቡለን ወረዳ ኤጳር ቀበሌ ጥቂት የፖሊስ ኃይሎችን የመደበ ቢሆንም ታጣቂዎቹ ሲመጡ ሸሽተው መጥፋታቸውን እንዳሳዘናቸው እና ሙያዊ መገለጫ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ ሕግ በማስከበር፣ ተጎጂዎችን የመካስ እና የማቋቋም ሥራ ይሰራልም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያሉት፡፡
ከሰሞኑ ዜጎችን ለሞትና መፈናቀል የዳረገ ጥቃት በተፈጸመበት መተከል ዞን ቡለን ወረዳ ጉብኝት ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ጥቃት የተፈጸመባቸው ሰዎች የሚካሱት ወንጀሉን የፈጸሙና የተባባሩ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል ነው ብለዋል፡፡
በጥቃቱ የተበታተኑ ቤተሰቦች በአጭር ጊዜ እንዲገናኙ፣ የተጎዱ ወገኖችም ሃይማኖታቸው በሚያዘው ልከ እንዲያርፉ መሥራት ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡
ከዕለት ምግብ አቅርቦት ጀምሮ እስከ ዘላቂ ማቋቋም ድረስ ያሉ እገዛዎች በፍጥነት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማስቻልና ወንጀሉን የፈጸሙና የተባበሩ አካላትንም በቁጥጥር ሥር ማዋል የቀጣይ ዐበይት ተግባራት መሆናቸውንም አቶ ደመቀ አስታውቀዋል፡፡
በተፈጸመው ወንጀል መንገድ የመራ፣ የጠቆመ፣ ያስፈጸመ፣ የተጠቂዎችን ንብረት ያወደመ፣ የዘረፈውን ሁሉ በዜጎች ጥብቅ ተሳትፎ ለሕግ የማቅረብ ሥራ ይጀመራል ስለማለታቸውም ነው አብመድ የዘገበው፡፡
“ወንጀለኞች ስለሸሹ የሚቀሩ አይደሉም”ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጠንካራ መርማሪ ቡድን በማቋቋም በሕግ መፋረድ የመንግሥት የቀጣይ የቤት ሥራ እንደሚሆንም ለተጎጂዎች ቃል ገብተዋል፡፡
ጥፋቱ እንዲፈጸም ከላይ እስከ ታች ያሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሚና ምን እንደነበር በጥልቀት ይመረመራል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ፣ በቸልተኝነትና በእንዝላልነት ጥቃቱ እንዲፈጸም ያደረጉ የሥራ ኃላፊዎች ላይ ፍትሕን ለመታደግ” እርምጃ እንደሚወሰድም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን ዐይን የሆነውን የሕዳሴው ግድብ ደኅንነት ለማረጋገጥ እና ለዜጎች ሰላምና ተጠቃሚነት ዘላቂነት እንዲኖረው የአካባቢውን የጸጥታ ኃይል አደረጃጀት ለማሻሻል መከላከያ በቅርበት ይሠራልም ተብሏል፡፡
በጉብኝቱ የሰላም ሚኒስትሯን ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል አደም መሀመድ እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው ጣሰው ተሳትፈዋል፡፡