ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ጃዋር መሃመድን ጨምሮ 24 ተጠርጣሪዎችን በሽብር እና ሌሎች ወንጀሎች ከሰሰ
እንደየተሳትፏቸው የተመሰረተ ነው የተባለው ክስ የፊታችን ሰኞ ለተከሳሾቹ እንደሚደርስም ታውቋል
ክሱ በ10 ተደራራቢ ክሶች የተመሰረተ ነው የተባለ ሲሆን መስከረም 6 መመስረቱም ተነግሯል
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጃዋር ሲራጅ መሀመድ፣ በቀለ ገርባ እና ሀምዛ አድናን እንዲሁም በሌሉበት የተከሰሱትን የኦሮሚያ ሜዲያ ኔትወርክ (OMN) ፣ ደጀኔ ጉተማ፣ ዶ/ር ብርሃነመስቀል አበበ እና ፀጋዬ ረጋሳን ጨምሮ በአጠቃላይ በ24 ሰዎች ላይ በመዝገብ ቁጥር 260215 10 ተደራራቢ ክሶች መመስረቱን አስታወቀ፡፡
ክሶቹ መስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት የተመሰረቱ ናቸው ያለው ዐቃቤ ህግ እንደየተጠርጣሪዎቹ ተሳትፎ መመስረታቸውንም ገልጿል፡፡
በ1996 የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 240 በመተላለፍ ብሔርን እና ሐይማኖትን መሰረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭት በመቀስቀስ፤ አንዱ ወገን በሌላው ወገን ላይ እንዲነሳሳ በማድግ፤ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 በመተላለፍ፤ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 761/2004 እና የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 በመተላለፍ በፈፀሙት ወንጀል ነው የተከሰሱት፡፡
ተከሳሾቹም መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀርበው ክሱ ይደርሳቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታውቋል፡፡