በእነ ጃዋር መሃመድ ላይ ተከፍቷል ከተባለው የክስ መዝገብ ጋር በተያያዘ በመጪው ሳምንት መግለጫ ሊሰጥ ነው
ክሱ በመጪው ሰኞ ለተጠርጣሪዎቹ ከተነበበ በኋላ ቀጥለው ባሉት ቀናት እንደሚሰጥም ነው የሚጠበቀው
መግለጫው በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የሚሰጥ ሲሆን የክሱ ዝርዝር መረጃዎች ለህዝብ የሚገለጹበት ነው ተብሏል
በእነ ጃዋር መሃመድ ላይ ተከፍቷል ከተባለው የክስ መዝገብ ጋር በተያያዘ በመጪው ሳምንት መግለጫ ሊሰጥ ነው
ጃዋር ሲራጅ መሀመድን ጨምሮ በአጠቃላይ በ24 ሰዎች ላይ በመዝገብ ቁጥር 260215 10 ተደራራቢ ክሶች ማስከፈቱን ያስታወቀው ጠቅላይ ዐቃቤ ጉዳዩን በማስመልከት በመጪው ሳምንት የመጀመሪያ ቀናት መግለጫ እንደሚሰጥ የአል ዐይን አማርኛ ምንጮች አመለከቱ፡፡
“ክስ መመስረት ባለበት ጊዜ ውስጥ ባለመመስረቱ ተከሳሾቹ ከሰኞ ጀምሮ ከእስር ሊለቀቁ ነው የሚል ወሬ በህዝብ ዘንድ ተሰራጭቷል” ያሉት ምንጮቹ መግለጫው ዐቃቤ ህግ ተቋሙ እየሰራ ያለውን ስራ ማህበረሰቡ እንዲያውቀው ለማድረግ የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ መከፈቱን በተመለከተ ዛሬ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ አጭር ጥቅል መረጃን ሰበር በሚል ርዕስ ሰጥቷል፡፡
ሆኖም ይህ ክስ መመስረቱን ለማሳወቅ ብቻ እንደሆነ ነው ምንጮቹ ለአል ዐይን የገለጹት፡፡
“አዋጅ ቁጥር 761/2004 ፣አዋጅ ቁጥር 1177/2012 ሲባል ምን ለማለት ነው” በሚል ስለ አጭሯ መግለጫ የሚያጠይቁት ምንጮቹ “ፍርድ ቤት ራሱ ክሱ በዝርዝር ሳይቀርብ እና ሳይነበብ ቀድሞ ለህዝብ ለሚዲያ መገለጹ ተገቢ አይደለም ማለቱ ስለማይቀር ክስ መመስረቱን ብቻ ለማሳወቅ ነው” ሲሉም ነው መግለጫው ተከፈተ የተባለውን ክስ የተመለከቱ ዝርዝር መረጃዎች ለህዝብና ለሚዲያ እንደሚሰጡበት የሚጠቁሙት፡፡
መግለጫው ክሱ ሰኞ ፍርድ ቤት ለሚቀርቡት ተጠርጣሪዎች ከተነበበ በኋላ በእለቱ አለበለዚያም ተከትለው ባሉት ቀናት ሊሰጥ ይችላል፡፡
“ለዚህም ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው፤ ሁሉም ሚዲያዎች ይጠራሉም” ተብሏል ምንጮቹ እንደሚያመለክቱት ከሆነ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉን አቶ ፍቃዱ ጸጋን ጨምሮ በምርመራው ላይ ተሳትፎ ያላቸው ፖሊሶች ተገኝተው ዝርዝር መረጃዎች እንደሚሰጡም ይጠበቃል፡፡
ዐቃቤ ህግ በጃዋር ሲራጅ መሀመድ፣ በቀለ ገርባ እና ሀምዛ አድናን እንዲሁም በሌሉበት የተከሰሱትን የኦሮሚያ ሜዲያ ኔትወርክ (OMN)፣ደጀኔ ጉተማ፣ዶ/ር ብርሃነመስቀል አበበ እና ፀጋዬ ረጋሳን ጨምሮ 10 ተደራራቢ ክሶች ማስከፈቱን መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡