ከንቲባቸው ክብደት እንዲቀንስ የሚያበረታቱት ነዋሪዎች
የጣልያኗ ከተማ ከንቲባ ከመሾማቸው በፊት 50 ኪሎ ግራም ይመዝኑ ነበር የተባለ ሲሆን ላይ 92 ኪሎ ደርሰዋል
የስራ ባህሪያቸው ለውፍረት ዳርጎኛል የሚሉት ከንቲባው ክብደታቸውን ለመቀነስ አዲስ ዘመቻ ጀምረዋል
ከንቲባቸው ክብደት እንዲቀንስ የሚያበረታቱት ነዋሪዎች
ሉቺያኖ ፍሬጎንስ የጣልያኗ ቫልዶቢያንዴ ከተማ ከንቲባ ናቸው።
እኝህ ከንቲባ ከ10 ዓመት በፊት ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ክብደታቸው ከ50 ኪሎ ግራም በታች ነበር ተብሏል።
ከአንድ ወር በተካሄደው ምርጫ ድጋሚ የከተማዋ ከንቲባ ተደርገው የተመረጡት እኝህ ከንቲባ አሁን ላይ ያላቸው ክብደት 90 ኪሎ ግራም ሆኗል።
ከንቲባው ክብደታቸውን ለመቀነስ ሲሉም በአካባቢው ወዳለ ተራራማ ስፍራ ለመንቀሳቀስ ማሰባቸውን ይፋ አድርገዋል።
"መጀመሪያ ላይ የኔ ጤና ያሳሰበው እና የቅርብ ሰው ክብደት መቀነስ እንዳለብኝ ነገረኝ፣ ከዚያ አብረን ለምን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ አናደርግም የሚል ሀሳብ መጣልኝ፣ ቆይቼ ሳስበው ደግሞ ይህ ነገር ለከተማችን ነዋሪዎችም ጥሩ ስለሚሆን እንዲቀላቀሉን ጥሪ አቀረብኩ" ብለዋል።
ከንቲባው እቅዳቸውን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ከንቲባቸውን ለማገዝ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
"ስንፍና፣ ያልተስተካከለ አመጋገብ እና የስራ ባህሪ ክብደት እንድጨምር አድርጎኛል" የሚሉት ከንቲባው ነዋሪዎች ላደረጉላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ነዋሪዎቹም ከንቲባቸውን አጅበው እስከ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ተጉዘዋል ተብሏል።
ከንቲባው እና የከተማዋ ነዋሪዎች በየሳምንቱ ሀሙስ ከሰዓት ተራራ የመውጣት ፕሮግራም የያዙ ሲሆን ከንቲባው የተባለውን ርቀት መንገድ መጓዝ አድካሚ እንደሆነባቸው ነገር ግን የግድ ማድረግ እንዳለባቸው ከዘጋርዲያን ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ላይ ተናግረዋል።
ከልክ በላይ ውፍረት በአውሮፓ ዋነኛ የማህበረሰብ ጤና ችግር ሲሆን የከንቲባው እና ነዋሪዎች ቅንጅት ትኩረት ስቧል።