የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር በሩሲያ ድምጽ አስመሳዮች መታለላቸው ተገለጸ
አውሮፓዊያን በዩክሬን ጦርነት መማረራቸውን ለሩሲያዊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ተናግረዋል
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በመደራደር ጦርነቱ እንዲቋጭ ፍላጎት መኖሩም ተገልጿል
የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር በሩሲያ ድምጽ አስመሳዮች መታለላቸው ተገለጸ፡፡
በቅጽል ስማቸው ቮቫን እና ልክሰስ የተሰኙት ሩሲያዊያን ድምጻቸውን በማስመሰል የሀገራት መሪዎችን እና ታዋቂ ሰዎችን በማዋራት ይታወቃሉ፡፡
ከሰሞኑ ደግሞ ለጣልያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጎርጊያ ሜሎኒ ራሳቸውን የአፍሪካ ዲፕሎማት አስመስለው ስልክ መደወላቸውን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ የአውሮፓ መሪዎች በዩክሬን ጦርነት ጉዳይ መማረራቸውን ተናግረዋል ተብሏል፡፡
አውሮፓዊያን ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በመደራደር ጦርነቱ እንዲቋጭ እንደሚፈልጉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ በሆነ ምክንያት ይህ ጦርነት እንዲቆም እንፈልጋለን እንዳሉም ተገልጿል፡፡
በጦርነቱ ጉዳይ ሁላችንም ደክሞናል፣ የዩክሬንም የመልሶ ማጥቃት በታሰበው ልክ ውጤታማ ሊሆን አልቻለም በሆነ መንገድ ከዚህ ጦርነት መውጣት እንፈልጋለን ሲሉም ተደምጠዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ፡፡
ዩክሬናዊያን የሚችሉትን እያደረጉ ነው የዓለም አቀፍ ህግን ባልጣሰ መልኩ ጦርነቱ በሰላም የሚጠናቀቅበት መንገድ መፈለግ አለበት ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
የቀድሞው የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር የዩክሬን ጦርነት ስለሚጠናቀቅበት መንገድ ፍንጭ ሰጡ
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ራሳቸውን የአፍሪካ መሪ እንደሆኑ ከደወሉላት ሩሲያዊያን ጋር ለ13 ደቂቃ በስልክ ቆይታ አድርገዋልም ተብሏል፡፡
የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስት ጽህፈት ቤት ቆይቶ ባወጣው መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በሩሲያዊያኑ ድምጽ አስመሳዮች በመታለላቸው መጸጸቱን አስታውቋል፡፡
ጽህፈት ቤታቸው አክሎም ጠቅላይ ሚኒስትሯ ስልኩን ያነሱት ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የተደወለላቸው መስሏቸው እንደሆነም ገልጿል፡፡
የጣልያን ፖለቲከኞች በጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ላይ ትችቶችን ሰንዝረዋል የተባለ ሲሆን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ማቲዮ ሬንዚ እና ጉሴፔ ኮንቴ ዋነኞቹ ናቸው፡፡
የቀድሞ የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትሮች እንዳሉት ጆርጂያ ሜሎኒ ተላላ ናቸው፣ ለጣልያናዊያን ያልነገሩትን እውነት ለሩሲያዊያን ተናግረዋል እና ሌሎችንም ትችቶችን ሰንዝረዋል፡፡
ሩሲያዊያኑ ድምጽ አስመሳዮች ከዚህ በፊት የዩክሬንን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪን ጨምሮ ሌሎች መሪዎችን በስልክ እየደወሉ ብዙ ሚስጢሮችን እና ሀሳባቸውን በማውጣጣት ይታወቃሉ፡፡