በጣልያን ተወስዳ የነበረችው የመጀመሪያ የኢትዮጵያ አውሮፕላን "ፀሐይ" አዲስ አበባ ገባች
በጣልያን መንግስት "ፀሐይ" አውሮፕላንን ለኢትዮጵያ ለመመለስ መስማማቱ ይታወሳል
"ፀሐይ" አውሮፕላን በ"አድዋ ድል መታሰቢያ" ሙዚየም እንደትቀመጥ ተደርጓል
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራችው "ፀሐይ" የሚል መጠሪያ የተሰጣት አውሮፕላን ትናንት ምሽት ላይ አዲስ አበባ መድረሷ ተነግሯል።
በጣሊያን ተወስዳ የነበችረው አውሮፕላን ባሳለፍነው ሳምንት ለኢትዮጵያ ተመልሳ መሰጠቷን ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ማስታወቁ ይታወሳል።
በፈረንጆቹ በ1935 በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ግዜ ተገጣጥማ በረራ ያደረገችው ፀሐይ አውሮፕላን ከበርካታ ዓመታት በኋላ ትናንት ምሽት አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ደርሳለች።
ከጣሊያን ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰችው "ፀሐይ" አውሮፕላን በ"አድዋ ድል መታሰቢያ" እንደትቀመጥ መደረጉም ተነግሯል።
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ "ፀሐይ" አውሮፕላንን በዛሬው ዕለት ተረክበው በዓድዋ ድል መታሰቢያ ለጎብኝዎች ምቹ በሆነ ስፍራ ማኖራቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው አስታውቀዋል።
"ፀሐይ" በኢትዮጵያ የተሰራችው የመጀመሪያ አውሮፕላን አውነታዎች
"ፀሐይ" በ1935 ዓ.ም ሄር ሉድዊግ ዌበር የተባለው ጀርመናዊ ኢንጂነር እና የንጉሱ ፓይለት በወቅቱ ከነበሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የተሰራች የመጀመሪያው አውሮፕላን ነች።
አውሮፕላኗ "ፀሐይ" የሚለውን ስያሜውም የቀዳማዊ ኃይለስላሴን ልጅ ልዕልት ፀሐይን ለማሰብ የተሰጠ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ፀሐይ ባለሁለት መቀመጫ እና ሁለትዮሻዊ መቆጣጠሪያ ያላት ብሎም የባለከፍተኛ ኃይል ሞተር ባለቤት ተደርጋ የተሰራች አውሮፕላን ነች።
"ፀሐይ" ኮምፓስ፣ የአብራሪ መቆጣጠሪያዎች፣ ሁለት ያለ ፍሬን ማቆሚያ የተገጠሙ የማረፊያ ሽክርክሪቶች እንደነበራም ተመላክቷል።
የ"ፀሐይ" አውሮፕላን ሞተር ባለሰባት ሲሊንደር ዋልተር ቪነስ ሲሆን የውሃ ማቀዝቀዣ ስርዓት የነበረው የ115 የፈረስ ጉልበት ባለቤትም ነበር።
"ፀሐይ" ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በፊት በኢትዮጵያ የተሰራች ብቸኛ አውሮፕላን ነበረች።
ፀሐይ በውስን ሃብት እና ስፍራ በጊዜው የነበሩትን አናፂዎች እውቀት እና የእጅ ጥበብ በመጠቀም የተሰራች አውሮፕላን ሲትሆን ፤ የ1930ዎቹ የአቪየሽን ጥረት ማሳያ ሆና የተረፈች አውሮፕላን ነች።