ናይጀሪያ በቪክተር ኦስሜን ጉዳይ ከጣልያን መንግሥት ጋር በመነጋገር ላይ መሆኗን አስታወቀ
የጣልያኑ ናፖሊ ክለብ አጥቂ የሆነው ኦስሜን ሆን ተብሎ ጥቃት እንደተከፈተበት ተገልጿል
ክለቡ ናፖሊ በበኩሉ በኦስሜን ላይ ለደረሰው ጥቃት ይቅርታ ጠይቋል
ናይጀሪያ በቪክተር ኦስሜን ጉዳይ ከጣልያን መንግሥት ጋር በመነጋገር ላይ መሆኗን አስታወቀች።
የናይጀሪያ ብሔራዊ ቡድን እና የጣልያኑ ናፖሊ እግር ኳስ ክለብ አጥቂ የሆነው ቪክተር ኦስሜን ከሰሞኑ የተቀናጀ የተባለ ጥቃት እየደረሰበት እንደሆነ ተገልጿል።
በዘንድሮው የሴሪ ኤ ውድድር ላይ ደካማ ጅማሮን እያደረገ ያለው ናፖሊ በደጋፊዎቹ ትችቶችን እያስተናገደ ይገኛል።
የአምናው የሴሪ ኤ አሸናፊው ክለብ ናፖሊ አጥቂው ኦስሜን ፍጹም ቅጣት ምት ስቷል እንዲሁም ግቦችን ማስቆጠር አልቻለም በሚል እየተተቹ ካሉ የክለቡ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሆኗል።
ይህ በዚህ እንዳለም በክለብ ይፋዊ የቲክቶክ ገጽ ላይ ቪክተር ኦስሜን ጎል ሲስት እና ደካማ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ተሰራጭተዋል።
በክለቡ ድርጊትም የተጫዋቹ ወኪል እና ኦስሜን ብስጭታቸውን የገለጹ ሲሆን ሁኔታው የተቀናጀ እና የተቀነባበረ ነው ተብሏል።
የናይጀሪያ ስፖርት ሚንስትር ጆን ኢኖህ ከጉዳዩ ዙሪያ ከጣልያን መንግሥት ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቹን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን ሲሉም ሚንስትሩ ተናግረዋል ተብሏል።
ክለቡ ናፖሊም በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ ያወጣ ሲሆን ለተፈጠረው አሳዛኝ ክስተት ይቅርታ ጠይቋል።
ክለቡ በመግለጫው ቪክተር ኦስሜን የናፖሊ ውድ ሀብት መሆኑን የገለጸ ሲሆን ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያደርግም አስታውቋል።
ተጫዋቹ ኦስሜን በክለቡ ድርጊት ማዘኑን ገልጾ የናፖሊን ማልያ ለብሶ የተነሳቸውን ፎቶዎች ከማህበራዊ ትስስር ገጾቹ ላይ አጥፍቷል።
ናፖሊ እግር ኳስ ክለብ ያለፈውን ውድድር ዓመት ከ26 ዓመት በኋላ ዋንጫ እንዲበላ ካደረጉ ተጫዋቾች መካከል ቪክተር ኦስሜን ትልቁን ድርሻ መወጣቱ ይታወሳል።