የቀድሞው የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር የዩክሬን ጦርነት ስለሚጠናቀቅበት መንገድ ፍንጭ ሰጡ
ምዕራባዊያን ሀገራት ለዩክሬን ጦር መሳሪያ መስጠት ቢያቆሙ ጦርነቱ እንደሚቆምም ተናግረዋል
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬን መልሶ ግንባታ ገንዘብ እንዲለግሱ ሲሊቪዮ ቤርሊስኮኒ ተናግረዋል
የቀድሞው የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር የዩክሬን ጦርነት ስለሚጠናቀቅበት መንገድ ፍንጭ ሰጥተዋል።
የቀድሞው የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሊቪዮ ቤርሊስኮኒ ካሳለፍነው የካቲት ወር ጀምሮ እየተካሄደ ስላለው ጦርነት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ቤርሊስኮኒ እንዳሉት ምዕራባዊያን ሀገራት ለዩክሬን የጦር መሳሪያ መርዳታቸውን ቢያቆሙ ከሩሲያ ጋር ወደ ድርድር ትመጣ እንደነበር ጠቅሰው ሀገራቱ ለመልሶ ግንባታ የሚውል ገንዘብ ቢለግሱ የተሻለ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
አሜሪካንን ጨምሮ የአውሮፓ ሀገራት ለዩክሬን በጦርነቱ ለደረሰባት ጉዳት ማካካሻ የሚሆን በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ለጣልያን ብዙሃን መገናኛዎች ያሉትን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ምዕራባዊያን ሰላም የሚፈልጉ ከሆነ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ መርዳታቸውን ሊያቆሙ ይገባል ብሏል፡፡
ዩክሬን በፈረንጆቹ 2014 በህዝበ ውሳኔ ወደ ሩሲያ ለተካለለችው ክሪሚያ እውቅና ልትሰጥ ይገባል የሚሉት ቤርልስኮኒ በሊሃንስክ እና ዶምብአስ ግዛቶች ደግሞ ምዕራባዊያን እና ተመድ በታዛቢነት የሚሳተፉበት አዲስ የህዝበ ውሳኔ ሊካሄድ ይገባልም ብለዋል፡፡
የ86 ዓመቱ ቤርሊስኮኒ ፎርዛ ኢታሊያ የተሰኘ ፓርቲን እየመሩ ሲሆን ፓርቲያቸው ከአንድ ሳምንት በፊት በተቋቋመው አዲስ የጣልያን ህግ አውጪ ምክር ቤት ድል የቀናው ሲሆን በቅርቡ የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑት ጆርጂያ ሜሎኒ ጋርም የጥምር መንግስት መስርተዋል፡፡
የቤርሊስኮኒን አስተያየት ተከትሎ የጣልያን ፖለቲከኞች በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትራቸው አስተያየት ላይ ትችቶችን ሰንዝረዋል፡፡
የቀድሞው የጣልያን ኢኮኖሚ ሚንስትር ካርሎ ካሌንዳ በትዊተር ገጻቸው ቤርሊስኮኒ የፑቲንነን ፕሮፓጋንዳ ሊያቆም ይገባል ሲሉ መጻፋቸው ተገልጿል፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲንን የሚጠቅም ፕሮፓጋንዳ ካላቆመ ፓርቲያቸው በውህደት ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ከመሰረተው አዲስ መንግስት የመውጣት አደጋ ሊደርስባቸው እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል፡፡