በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በአለም በአማካይ 24 ሚሊዮን ሰዎች በአመት እንደሚፈናቀሉ ተገለጸ
በምስራቅ አፍሪካ 637 ሺህ ሰዎች በዚሁ ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸዋል
በ2023 በጎርፍ አደጋ ብቻ 9.8 ሚልየን ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል
ከጦነት እና ሽብርተኝነት ቀጥሎ የምድር ስጋት የሆነው የአየር ንብረት ለውጥ በአለም አቀፍ ደረጃ በበዙ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡
በመካከለኛ ገቢ ባላቸው እና በድሀ ሀገራት ክንዱ የሚበረታው የአየር ንብረት ለውጥ ወትሮም ቢሆን የተቃና ኑሮ የሌላቸውን ዜጎች ህይወት በእጅጉ አክብዷል፡፡
እንደ ተመድ የስደተኞች ኮሚሽን መረጃ የጎርፍ፣ የመሬት መንሸራት እና ሌሎችም የተፈጥሮ አደጋዎች የሚደርሱባቸው አንዳንድ ቦታዎች ቀደም ብሎም ቢሆን ተፈናቃዮች የሚኖሩባቸው መሆናቸው ሁኔታውን አክፍቶታል።
በቅርቡ በአፍጋኒስታን በብራዚል እና በምስራቅ አፍሪካ የተከሰቱ ጎርፎች የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በማውደም የሰዎችንም ህይወት ቀጥፈዋል፡፡
የተመድ የስደተኞች ከሚሽን ባለፉት አስርተ አመታት በተፈጥሮ አደጋዎች በአማካይ 24 ሚሊዮን ሰዎች በየአመቱ ከቀያቸው እንደተፈናቀሉ ሲገልጽ በ2023 አመት ብቻ ደግሞ 9.8 ሚልየን ሰዎች መኖርያቸውን ጥለው ለመሰደድ መገደዳቸውን አስታውቋል፡፡
በቅርብ ጊዜ የተፈጥሮ አደጋ ተከስቶባቸው ከፍተኛ ጉዳት ያስተናገዱ ሀገራት
1.አፍጋኒስታን
ከሁለት አስርት አመታት በላይ በጦርነት ውስጥ በሰነበተችው አፍጋኒስታን ከፍተኛ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በፈጠረው አደጋ ከ300 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። በትምህርት ቤቶች፣ በ2000 መኖርያ ቤቶች ፣ በጤና ተቋማት ላይ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ላይ የከፋ አደጋ አድርሷል፡፡
በመጪዎቹ ሳመንታት በማዕከላዊ እና ደቡብዊ አፍጋኒስታን ተጨማሪ ከፍተኛ ዝናብ እና የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል የሜትሮዎሎጂ ድርጅቶች እያስጠነቀቁ ነው፡፡
2. ብራዚል
በደቡባዊ ሪዮ ግራንዴ ዶሱል ግዛት ያጋጠመው የጎርፍ አደጋ የ161 ሰዎች ህይወትን ሲነጥቅ በ2.34 ሚልየን ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡
ከነዚህ መካከከል አለም አቀፍ ከለላ የሚሹ 43ሺህ የሃይቲ እና ቬንዚዌላ ስደተኞች ይገኙበታል፡፡ በአደጋው 90 በመቶ የግዛቷ መዘጋጃቤታዊ አገልግሎቶች ከስራ ውጭ ሲሆኑ 582ሺ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡
3. ምስራቅ አፍሪካ
በ11 ሀገራት 4.6 ሚልየን ስደተኞችን በሚያስተናግደው በዚህ ቀጠና የኤል ኒኖ ከፍተኛ ዝናብ ከመጋቢት ጀምሮ ያስከተለው የተፈጥሮ አደጋ በ637 ሺ ሰዎች ላይ ጉዳት አስከትሏል። ከነዚህ ውስጥ 234ሺዎቹ ቀያቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡ በኬንያ፣ ብሩንዲ፣ ሶማሊያ እና ታንዛኒያ ደግሞ 210 ሰዎች ሞተዋል
የተመድ የስደተኞች ከሚሽን እንደሚለው ከሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ በግጭት ምክንያት የተሰደዱ እና የውስጥ ተፈናቃይ የሆኑ 60 በመቶ ወይንም 114 ሚልየን ሰዎች በነዚህ በተፈጥሮ አደጋዎች በተደጋጋሚ በሚመቱ አካባቢዎች ይኖራሉ