ጥንዶቹ 362 ሺህ ኪ.ሜ በመኪና መጓዝ 102 ሀገራትን አዳርሰዋል
የሰው ልጆች በህይወት ዘመናቸው ብናደርገው ያስደስተናል የሚሉትና እንደ መርህ ኖረውት ለማለፍ የሚፈልጉት ያልተለመደ ነገር ሲያከናውኑ ማየትና መስማት የተለመደ ነው።
ሶሞኑን የተለያዩ የሚዲያ አውታሮች አጀንዳ አድረገው በመቀባበል ላይ ያሉትንና “ላለፉት 22 ዓመታት በመኪና ዓለምን ዞረዋል የተባለው የአርጀንቲና ቤተስብ” የዚሁ አንድ አካል ነው።
ጊዜው የዛሬ 22 ዓመታት ነው፤ “ግራሀም ፒግ” የተሰኘችው እምብዛም ለጉዞ የማትመረጠው የ1928 ሞዴል መኪና የያዙ አርጀንቲናዊያን ጥንዶቹ 4 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ብቻ በመያዝ ከአርጀንቲና ወደ አላስካ ጉዞ መጀመራውን የኤ.ኤፍ.ፒ ዘገባ ያመለክታል።
በአሜሪካ ሰሜን ምዕራብ ወደ ምትገኘው አላስካ ጉዞው አንድ ብሎ የጀመረው ቤተሰብ ታዲያ በቀላሉ ወደ ቦነስአይረስ የሚመለስ አልነበርም።
ከጅምሩ ትልቁን አልሞ ከአርጀንቲና የተነሳው የአርጅንቲናውያኑ ጥንዶች “የሄርማን ቤተሰብ” ላለፉት 22 ዓመታት፤ በመኪና ጉዞ ዓለምን ሲያካልል መቆየቱ ነው የተነገረው።
በቀን ለጥቂት ሰዓታት ብቻ መጓዝ በምትችለው መኪና ሲጓዝ የነበረው ቤተሰብ እያፈራረቀም ቢሆን በ22 ዓመታት 362 ሺህ ኪሎ ሜትር በመጓዝ 102 ሀገራትን አዳርሷል።
ቤተሰቡ 22 ዓመታት የፈጀበት የመኪና ጉዞ በስድስት ወራት ብቻ ሊጠናቀቅ ይችል የነበረ መሆኑ ነው።
ይሁን እንጂ ለመኪናው ልዩ ፍቅር ያለው ሄርማን “መኪናው ማቀዝቀዣ የሌላትና መቀመጫዎቹ ምቹ ባይሆኑም ጉዞው አስደናቂ ነበር” ሲል ተናግሯል፡፡
በቀን ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ የማይችለው መኪናው እንደፈረንጆቹ ጥር 25 ቀን 2000 የስፔር ለውጦች እንደተደረጉለትም ሄርማን አክሏል።
የሄርማን ቤተሰብ የ1928 ሞዴሏን ‘’ግራሀም ፒግ’’ መኪና የሚጠቀምባት ለጉዞ ብቻ አልነበርም፤ መኪናዋ ቤተሰቡ ልጆች ያፈራባት መኖርያ እና ማደርያ ጭምርም ነበረች።
ጥንዶቹ ዓመታት በፈጀው ጉዟቸው ልጆች ያሉበት ቤተሰብ መመስረት ችለዋል።
ጥንዶቹ በአሜሪካ፣ አርጀንቲና፣ ካናዳ እና አውስትራሊያ በነበራቸው ጉብኝት ባምባ፣ ቴሂዮ፣ ጃሎማ እና አላቢ የተባሉ የ19፣16፣14 እና 12 ዓመት ልጆችም አፍርቷል።
መኪናው ለቤተሰቡ እንደመኖሪያ ቤት ሆኖ ሲያገለግል ነበር የሚሉት ጥንዶቹ፤ ራሳቸውን በመኪና ውስጥ እንዲሁም ልጆቻቸው በጣሪያው ላይ በድንኳን እየተኙ ዓመታት እንደዘለቁም ገልፀዋል፡፡
ጉዟቸውን ለዓመታት በባህር ዳርቻዎች፣ ተራራዎች እንዲሁም ሀይቆች በማድረግ ያሳለፉት ጥንዶቹ ፤ በተለያዩ ወቅቶች ፈታኝ የሚባሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎችም አሳልፈዋል።
የጥንዶቹ ቤተሰብ “አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ግጭቶች እና ቀውሶች፣ በእስያ ተንሰራፍቶ የነበረው የወፍ ጉንፋን፣ በአፍሪካ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሺኝ እና ወባ በጉዟችን ያጋጠሙን ፈተናዎች ነበሩ” ብለዋል።
ጥንዶቹ በየሶስት አመት ወደ አርጀንቲና በመመለስ ለሁለት ወይም ለሶስት ወራት ዘመዶቻቸውን ይጎበኙ እንደነበርም ገልጸዋል።
በሁለት አስርት ዓማታት ጉዟቸው ከከተቧቸው ጽሁፎች 100 ሺህ የመፅሀፍ ቅጂዎችን እንደሸጡም ጭምር ተናግረዋል።