ጣሊያን ቻትጂፒቲ ጥቅም ላይ እንዳይውል በማገድ ቀዳሚዋ አውሮፖዊ ሀገር ሆነች
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂው የግለሰቦችን መረጃ የሚሰበስብበት መንገድ የሀገሪቱን ህግ ጥሷል በሚል ነው የታገደው
የቻትጂፒቲ ደንበኞች መረጃ ከ10 ቀናት በፊት ተጠልፎ መውጣት መነጋገሪያ እንደነበር ይታወሳል
ጣሊያን የአሜሪካውን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ቻትጂፒቲ በሀገሪቱ ጥቅም ላይ እንዳይውል ማገዷ ተነገረ።
የጣሊያን የመረጃ ጥበቃ ተቋም ቻትጂፒቲ የደንበኞቹን መረጃ የሚሰበስብበት ስርአት የጣሊያንን ህግ የማያከብር በመሆኑ ታግዷል ብሏል።
በዚህም ሮም ቻትጂቲን ያገደች የመጀመሪያዋ የአውሮፓ ሀገር ሆናለች።
በካሊፎርኒያ መቀመጫውን ያደረገው ኦፕንኤአይ ኩባንያ ንብረት የሆነው ቻትጂፒቲ በተዋወቀ በሁለት ወራት ውስት ከ100 ሚሊየን በላይ ደንበኞች ማፍራት ችሏል።
ከባድ ፈተናዎችን ከመስራት እስከ የግብር ሂሳብ ማወራረድ የማይሰራው ነገር የለም የተባለለት ሰው ሰራሽ አስተውሎትን የሚጠቀም ቴክኖሎጂ ከ10 ቀናት በፊት የደንበኞቹ መረጃ አፈትልኮ መውጣት ግን ጥርጣሬ እንዲፈጠርበት አድርጓል።
ጣሊያንም የቻትጂፒቲ ደንበኞች የፍለጋ ታሪክን ጨምሮ የባንክ እና ተያያዥ ሚስጢራዊ ሰነዶች መውጣት ብቻ ሳይሆን በርካታ የሚያሳስቡኝ ነገሮች አሉ በሚል በጊዜያዊነት አግዳዋለች።
ቴክኖሎጂው የግለሰቦችን መረጃ ሰብስቦ የሚይዝበት ስርአትን እየመረመረ የሚገኘው የሀገሪቱ መንግስት፥ ቻትጂፒቲ የሚያስቀምጠው የእድሜ ገደብ አለመኖሩንም ሌላው ጥያቄ የሚያስነሳበት ጉዳይ ነው ብሏል።
የእድሜ ገደብ አለመኖሩ ቴክኖሎጂው ሊሰጥ የሚችለው የተሳሳተ መልስን እንደትክክል የሚወስዱ ታዳጊዎች የነገ ህይወት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራልም ነው ያለው።
የሀገገሪቱ የመረጃ ጥበቃ ተቋም ቻትጂፒቲ በ20 ቀናት ውስጥ ላሳሰበኝ ጉዳይ ምላሽ ካልሰጠ 21 ሚሊየን ዶላር ቅጣት እንደሚጠብቀው ማሳሰቡንም የአሜሪካው ኤን ፒ አር ዘግቧል።
ቻትጂፒቲን በማገድ ጣሊያን የመጀመሪያዋ ሀገር ናት፤ አሜሪካም መሰል እርምጃ ልትወስድ ትችላለች የሚለው ዘገባው በፍጥነት ተቀባይነት ያገኘውን ቴክኖሎጂ ሌሎች ሀገራትም ጥቅም ላይ እንዳይውል ሊያደርጉ እንደሚችሉ አመላክቷል።
አሜሪካ የቻይናውን ቲክቶክ በስለላ እንደምትጠረጥረው ሁሉ ቻይናም የአሜሪካውን ቻትጂፒቲ በመሰል ክስ ልታግደው እንደምትችል ተነግሯል።