ተጠቃሚዎቹ አገልግሎቱ ከህመም ይልቅ ጭንቀትን የሚያራግፍ ሆኖ አግኝተነዋል ብለዋል
ፈጣን ምግቦችን ከጥፊ ጋር የሚያቀርበው የጃፓን መጠጥ ቤት ትኩረት ስቧል።
ናጎያ በተሰኘችው ከተማ የሚገኘው ምግብ ቤት አወዛጋቢውን አገልግሎት መጀመሩ በርካታ ደንበኞችን አትርፎለታል ተብሏል።
በአንዲት ሴት ብቻ አገልግሎቱን የጀመረው ምግብ ቤት በደንበኞች መብዛት ምክንያት እጃቸውን ለጥፊ ዝግጁ የሚያደርጉ ሰራተኞቹን አበራክቷል።
ከምግብ ወይም መጠጥ በፊት በጥፊ መጭል የፈለገ ተጠቃሚ የሚመታውን መርጦ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላልም ነው የተባለው።
ላይቤሪቲ ታይምስ የተሰኘው የቻይና መገናኛ ብዙሃን “ኢዛካያ” የሚል ስያሜ ያለውን ምግብ ቤት የተለየ አገልግሎት በምስል አስደግፎ ይዞ ወጥቷል።
ለአንድ ጥፊ እስከ 100 የጃፓን የን የሚጠይቀው “ኢዛኪያ” በመረጧት እንስት በጥፊ ፊችአው እስኪቀላ መመታት ከሚፈልጉ ደንበኞቹ እስከ 500 የን ክፍያ እንደሚጠይቅ ነው ዘገባው የጠቀሰው።
አገልግሎቱን የሚጠቀሙ ሰዎች ዘና የማለት ስሜት እንደተሰማቸው እንደነገሩትና በጥፊ የሚመቷቸውን ሴቶች ሲያመሰግኑ መመልከቱንም የላይቤሪቲ ታይምስ ዘጋቢ ገልጿል።
የጥፊ መምታት አገልግሎቱ የቀልድ አለመሆኑንም በቀጣዩ ተንቀሳቃሽ ምስል አጋርቷል።
መጠጥ ቤቱ ከሚያቀርበው መደበኛ አገልግሎት ይልቅ ጥፊው ትኩረት መሳቡን ተከትሎ “ደንበኞቼን በጥፊ ማጮል በቃኝ” የሚል መግለጫ እንዲያወጣ አስገድዶታል።
“አገልግሎታችን የሚያሳዩ ቆየት ያሉ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ትኩረት መሳባቸው አስገርሞናል፤ አሁን ግን ደንበኞቻችን በጥፊ ለመመታት ወደኛ መምጣት የለባቸውም” የሚል መልዕክቱንም ነው በትዊተር ገጹ ላይ ያጋራው።
ይሁን እንጂ በሀገረ ጃፓን ከምግብ እና መጠጥ ጋር ጥፊ የሚያቀርበው ምግብ ቤት አሁንም ድረስ በደንበኞች እየተጨናነቀ ነው ሲል ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።