የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር በኦንላይን በተለቀቀው ሀሰተኛ የወሲብ ቪዲዮ ምክንያት ካሳ ጠየቁ
ሜሎኒ በስም ማጥፋት ጉዳይ በፈረንጆቹ ሐምሌ ሁለት ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸወን ይሰጣሉ ተብሏል
ጆርጂያ ሜሎኒ እሳቸውን የሚያሳይ ሀሰተኛ የወሲብ ቪዲዮ በኦንላይን ከሚሊዮን ጊዜ በላይ መታየቱን ተከትሎ የ100ሺ ዩሮ ካሳ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል
የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር በኦንላይን በተለቀቀው ሀሰተኛ የወሲብ ቪዲዮ ምክንያት ካሳ ጠየቁ።
የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ እሳቸውን የሚያሳይ ሀሰተኛ የወሲብ ቪዲዮ በኦንላይን ከሚሊዮን ጊዜ በላይ መታየቱን ተከትሎ የ100ሺ ዩሮ ካሳ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ቢቢሲ የጣሊያን ሚዲያዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ መርማሪዎች አንድ የ40 አመት ግለሰብ እና የ73 አመት እድሜ ያለው አባቱ በረቀቀ መንገድ(ዲፕፌክ) የሜሎኒን ፊት ሌላ ሰው አካል ላይ በመለጠፍ ሀሰተኛ የወሲብ ቪዲዮ ማዘጋጀታቸውን እና ማሰራጨታቸውን ስላረጋገጡ በስም በማጥፋት ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ይህ ቪዲዮ መቀመጫውን አሜሪካ ባደርገው የፖርኖ ሳይት በርካታ ሚሊዮን ጊዜ መታየቱን ዘገባው የጣሊያን ዜና አገሌግሎትን ጠቅሶ ዘግቧል።
ሜሎኒ በስም ማጥፋት ጉዳይ በፈረንጆቹ ሐምሌ ሁለት ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸወን ይሰጣሉ ተብሏል።
የጠቅላይ ሚኒስትሯ ጠበቃ በሜሎኒ የተጠየቀው የ100ሺ ዩሮ ወይም የ108 ሺ ዶላር ካሳ ተምሳሌታዊ እንደሚሆን እና ክሱን የሚያሸንፉ ከሆነ ጥቃት ለደረሰባቸውን ሴቶች ድጋፍ እንደሚያውሉት ተናግሯል።
ሜሎኒ ባቀረቡት ቅሬታ "እንዲህ አይነት ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ክስ ከማቅረብ ወደኋላ እንዳይሉ" የሚል መልዕክት ማስተላለፍ እንደሚልጉም ገልጸዋል።