ትራምፕ በጆርጂያ የምርጫ ውጤት ለማስቀየር በመሞከር ወንጀል ተከሰሱ
በ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሚሳተፉት የቀድሞው ፕሬዝዳንት በዚህ አመት 4ኛ የወንጀል ክስ ነው የቀረበባቸው
የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ክሱን ያጣጣለው ሲሆን፥ አሜሪካ ወደ አምባገነናዊ ስርአት እያመራች ነው ብሏል
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጆርጂያ ግዛት የምርጫ ውጤትን ለማስለወጥ ተንቀሳቅሰዋል በሚል ተከሰሱ።
የፉልተን ካውንቲ አካባቢ አቃቤ ህግ ፋኒ ዊልስ ከየካቲት 2021 ጀምሮ ትራምፕና አጋሮቻቸው በምርጫ ጣልቃገብነት እንዲከሰሱ ሲያአርጉት የነበረው ምርምራ ተጠናቆ ክስ እንዲመሰረትባቸው ተወስኗል።
በዚህም የቀድሞው ፕሬዝዳንት እና 18 አጋሮቻቸው 41 የወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን፥ 13ቱ በትራምፕ ላይ ያተኮሩ ናቸው ተብሏል።
ክሱ ሪፐብሊካኖች ከፍተኛ መራጭ ያገኙባት በነበረችው ጆርጂያ የድምጽ ማጭበርበር እንዲካሄድ ተደርጓል ይላል።
ባለ98 ገጹ ክስ ትራምፕ ለጆርጂያ ግዛት ከፍተኛ የምርጫ ሃላፊ ብራድ ራፈንስበርግ ጋር ደውለው በጆርጂያ ያጡትን ድምጽ ማግኘት የሚያስችል ስራ እንዲሰራ መጠየቃቸውን ያመላክታል።
በአጠቃላይ በ2020ው ምርጫ አሸንፌያለው ብለው ከማወጃቸውና ደጋፊዎቻቸው በካፒቶል ሂል ከፈጠሩት ግርግር ጋር በተያያዙት ክሶች ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሏል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት በዚህ አመት የወንጀል ክስ ሲመሰረትባቸው ይህ ለአራተኛ ጊዜ ነው።
ትራምፕና ሌሎች 18 ተከሳሾች ነሃሴ 25 2023 ላይ ራሳቸው በፈቃዳቸው ፍርድ ቤት ካልቀረቡ በቁጥጥር ስር እንደሚውሉ ክሱን ያቀረቡት ፋኒ ዊልስ መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።.
የትራምፕ ጠበቆች ክሱን ህገመንግስቱን ያላከበረና ፖለቲካዊ ፍላጎት የተንጸባረቀበት ነው በሚል አጣጥለውታል።
የ2024 የምርጫ ቅስቀሳ ቡድናቸውም በቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ እየቀረቡ ያሉ ክሶች አሜሪካ ወደ አምባገነናዊ ስርአት እየትሸጋገረች መሆኑን ማሳያ አድርጎ አቅርቦታል።
በጆርጂያ የቀረበው ክስ ትራምፕ በ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዳግም ለመመረጥ የጀመሩትን ቅስቀሳ ለማዳከም ያለመ የፖለቲካ ቁማር መሆኑንም በመጥቀስ።
ዶናልድ ትራምፕ እየቀረቡባቸው ያሉ ክሶች በቀጣዩ አመት ምርጫ ከገለልተኛ መራጮች ድምጽ የማግኘት እድላቸውን ሊያጠበው እንደሚችል ሬውተርስ የሰበሰበው የህዝብ አስተያየት ያሳያል።