የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ወሲባዊ አስተያየት ከሰጠው አጋራቸው ጋር ተለያዩ
ጋዜጠኛ አንድሪያ ጊያምቡሩኖ በቅርቡ በሰጠው ወሲባዊ አስተያየቱ ትችት ተሰንዝሮበታል
"ከአንድሪ ጊያምቡርኖ ጋር ለ10 አመታት የነበረኝ ግንኙነት እዚህ ላይ ያበቃል" ሲሉ ሜሎኒ በማህበራዊ ሚዲያ አካውንታቸው ላይ ጽፈዋል
የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ወሲባዊ አስተያየት ከሰጠው አጋራቸው ጋር ተለያዩ።
የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ጋዜጠኛ የሆነው አጋራቸው በቴሌቪዥን ላይ በሰጠው ወሲባዊ አስተያየት ምክንያት እንደተለዩት ሮይተርስ ዘግቧል።
ጋዜጠኛ አንድሪያ ጊያምቡሩኖ በቅርቡ በሰጠው ወሲባዊ አስተያየቱ ትችት ተሰንዝሮበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ በጊያምቡርኖ አስተያየት መለካት እንደሌለባቸው እና ወደፊት እሱን የተመለከቱ ጥያቄዎች እንደማይመልሱ ባለፈው ወር ለጋዜጠኞች ተናግረው ነበር።
የ46 አመቷ ሜሎኒ መለያየታቸውን ይፋ ያደረጉት በቀኝ ዘመም ጥምረት መንግስት ቢሮ አንደኛ አመት የስልጣን ዘመናቸውን ባከበሩበት ወቅት ነው።
"ከአንድሪ ጊያምቡርኖ ጋር ለ10 አመታት የነበረኝ ግንኙነት እዚህ ላይ ያበቃል" ሲሉ ሜሎኒ በማህበራዊ ሚዲያ አካውንታቸው ላይ ጽፈዋል።
ሜሎኒ አክለውም "ጉዟችን የሆነ ጊዜ ተለያይቷል፤ ይህን አሜን ብሎ መቀበያው ጊዜ አሁን ነው"ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ እንደተናገሩት በግል ህይወታቸው ያጋጠማቸው ችግር የሚፈልጉትን አላማ እንዳያሳኩ አላደናቀፋቸውም።
በፈረንጆቹ በ2014 በቴሌቪዥን ስቱዲዮ የተገናኙት ጥንዶቹ የሰባት አመት ሴት ልጅ አፍርተዋል።
የ42 አመቱ ጊያምቡርኖ ሚዲያሴት በተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ በሚተላለፍ ፕሮግራም ላይ አቅራቢ ሆኖ ይሰራል።
ጊያምቡርኖ በዚህ ሳምንት በሰራው ሌላ ፕሮግራም ላይ ተገቢ ያልሆነ የሰውነት ክፍሉን ሲነካካ፣ ነውር የሆነ ቋንቋ ሲጠቀም እና ወደ ሴት ባልደረባው ሲሄድ ታይቷል።
ባልደረባውንም "ለምን ቀደም ብየ አላገኘሁሽም?" ሲልም ይጠይቃታል።
በሁለተኛው አየር ላይ በተላለፈው የድምጽ ቅጅ ጊያምቡርኖ እሷን እንደወደዳት እና የሴት ጓደኞቹ በቡድን ወሲብ የሚሳተፉ ከሆነ ከእሱ ጋር እንዲሰሩ እንደሚፈቅድላቸው ሲናገር ይደመጣል።
የቴሌቪዥን ጋዜጠኛው ጊያምቡርኖ በንግግሩ በነሐሴ ወር ከፍተኛ ትችት ቀርቦበት ነበር።
ተቃዋሚው ዲሞክራቲክ ፖርቲ የጊያምቡርኖ አስተያየት "ትምክተኛ፣ ወሲባዊ እና ምቾት የማይሰጡ ናቸው" የሚል ትችት ሰንዝሮ ነበር።