በአፍሪካ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ጃክ ማ ከኢትዮጵያ ጋር ተባብረው ሊሰሩ ነው
በአፍሪካ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ጃክ ማ ከኢትዮጵያ ጋር ተባብረው ሊሰሩ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ ጠዋት ከቻይናዊው ቢሊየነር ጃክ ማ ጋር በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስን (COVID19ን) ስርጭት ለመግታት በጋራ መስራት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ተወያይተው መስማማታቸውን ገልጸዋል።
ለእያንዳንዱ የአፍሪካ ሀገር ከ10 ሺህ እስከ 20 ሺህ የሚደርሱ ኮሮናን መመርመሪያ ኪቶችን እና 100 ሺህ ማስኮችን ለማሰራጨት ጃክ ማን ከኢትዮጵያ ጋር ለመተባበር መምረጣቸውንም ይፋ አድርገዋል።
እስካሁን ኢትዮጵያን ጨምሮ 18 የአፍሪካ ሀገራት የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው ሪፖርት አድርገዋል፡፡
የስፔን ቀዳማዊት እመቤት በኮሮና ቫይረስ ተያዙ
የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ባለቤት ቤጎና ጎሜዝ በቫይረሱ መያዛቸውን የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ባለቤታቸው በመልካም ጠየንነት ላይ እንደሆኑና ማድሪድ በሚገኘው ቤታቸው እንደሚገኙም ጽ/ቤቱ አስታውቋል፡፡ ሁለት የሀገሪቱ ሚኒስትሮችም በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ከቫይረሱ ነጻ ናቸው ተባለ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባደረጉት ምርመራ ከኮሮና ነጻ መሆናቸው መረጋገጡን ነጩ ቤተመንግስት ይፋ አድርጓል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ከሰሞኑ ካገኟቸው ግለሰቦች መካከል በተወሰኑት ላይ ቫይረሱ ከመገኘቱ ጋር በተያያዘ ብዙ ሲወራባቸው ከመሆኑም ባለፈ እርሳቸውም ለመመርመር አሻፈረኝ ብለው ቆይተው ነበር፡፡
ዩ.ኤስ አሜሪካ በቫይረሱ በከፍተኛ መጠን ከተጠቁ ሀገራት አንዷ ስትሆን በሀገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች ቁጥር 3,000 ገደማ ሲደርስ ከ60 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሆቴሉን የኮሮና ቫይረስ መታከሚያ አደረገ
የፖርቹጋልና የጁቬንቲዩስ የመስመር አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በትውልድ ሃገሩ የሚገኘውን ሆቴሉን ለኮሮና ወይም ለኮቪድ 19 ተጠቂዎች መታከሚያ እንዲሆን ማድረጉ ተገለጸ፡፡
ከሰሞኑ በትዉልድ ሃገሩ ፖርቹጋል በቫይረሱ ስጋት ራሱን ለይቶ የሚገኘው ክርስቲያኖ ሆቴሉን ወደ ህክምና መስጫ ቦታነት መቀየሩ እያስመሰገነው ነው፡፡
የክርስቲያኖ ሮናልዶ የክለብ አጋሩ ዳንኤል ሩጋኒ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ክርስቲያኖም በትውልድ ሃገሩ እንደሚቆይ ነው የተገለጸው፡፡
እስካሁን ከ 6,000 በላይ ተጠቂዎች የሚገኙባት ስፔን 193 ሰዎች ሞተውባታል፡፡