ሰሜን ኮሪያ በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ሚሳኤሎችን አስወነጨፈች
ፒዮንግያንግ የዩራኒየም ማብለያ ጣቢያዋን ለመጀመሪያ ጊዜ ባሳየች ማግስት ነው የባለስቲክ ሚሳኤሎችን የሞከረችው
ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ የሰሜን ኮሪያን ድርጊት “የማንታገሰው ነው” በሚል ተቃውመውታል
ሰሜን ኮሪያ በርካት አጭር ርቀት ተምዘግዛጊ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን አስወነጨፈች።
ከፒዮንግያንግ በስተሰሜን ከምትገኘው ካኦቺን የተነሱት ሚሳኤሎች ወደ ምስራቅ አቅጣጫ 400 ኪሎሜትሮችን መምዘግዘጋቸውን ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ገልጸዋል።
ሀገራቱ ሰሜን ኮሪያ በዛሬው እለት ምን ያህል ሚሳኤሎችን እንዳስወነጨፈች ግን አልጠቀሱም።
ሙከራው የኮሪያ ልሳነ ምድርን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ያለችው ደቡብ ኮሪያ፥ ፒዮንግያንግ ጸብ አጫሪ ድርጊቷን ከቀጠለች ተገቢውን የአጻፋ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነኝ ብላለች።
የጃፓን የባህር ዘብ የመጀመሪያው የሚሳኤል ሙከራ ከታወቀ ከ30 ደቂቃ በኋላ ሰሜን ኮሪያ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን አከታትላ መተኮሷን ገልጿል።
በተተኮሱት ሚሳኤሎች ቢያንስ አንዱ በሀገሪቱ ሰሜን ምስራቃዊ የባህር ዳርቻ ማረፉን በመጥቀስም ሙከራው “ፍጹም የምንታገሰው” አይደለም ነው ያለው በመግለጫው።
የአሜሪካ የኢንዶ ፓስፊክ እዝም የፒዮንግያንግ የባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራን እንደሚያውቅ እና ከሴኡልና ቶኪዮ ጋር እየመከረበት መሆኑን በኤክስ (ትዊተር) ገጹ ላይ አስፍሯል።
ሰሜን ኮሪያ በዛሬው እለት የፈጸመችው የሚሳኤል ማስወንጨፍ ሙከራ በአንድ ሳምንት ውስጥ ሁለተኛው ነው።
ፒዮንግያንግ ባለፈው ሀሙስ ከሁለት ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አጭር ርቀት ተምዘግዛጊ ባለስቲክ ሚሳኤል ማስወንጨፏ ይታወሳል።
ሴኡል ይህን ሙከራ ለሩሲያ የሚላክ መሳሪያ የተፈተሸበት ሊሆን እንደሚችል መግለጿን ሬውተርስ አስታውሷል።
ከሩሲያ ጋር ወታደራዊ ትብብሯን እያጠናከረች የምትገኘው ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ አጭር ርቀት የሚጓዙ ሚሳኤሎችን እየላከች ነው የሚል ተደጋጋሚ ክስ ይቀርብባታል። ምንም እንኳን ፒዮንግያንግም ሆነች ሞስኮ የአሜሪካ እና አጋሮቿን ወቀሳ ቢያጣጥሉትም።
ሰሜን ኮሪያ በዛሬው እለት አጭር ርቀት ባለስቲክ ሚሳኤል የሞከረችው በምዕራባውያን የተገለለችው ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ የዩራኒየም ማበልጸጊያ ጣቢያዋን ካሳየች በኋላ ነው።
ጣቢያውን የተመለከቱት ኪም ጆንግ ኡን ዩራኒየም የማበልጸግ ሂደቱ እንዲፋጠን ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው።