ዚምባቡዌ በድርቅ ምክንያት ለረሃብ የተጋለጡ ዜጎቿን የዝሆን ስጋ ልትመግብ ነው
ሀገሪቷ ከፍተኛ ረሃብ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች 200 ዝሆኖችን ለማረድ በዝግጅት ላይ ነች ተብሏል
ከ200 ሺህ በላይ ዝሆኖች የሚገኙባቸው የደቡብ አፍሪካ ሀገራት በአለም ላይ በርካታ ዝሆኖች ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች መካከል ይጠቀሳሉ
ዚምባቡዌ ከአስርት አመታት ወዲህ ባጋጠማት አስከፊ ድርቅ የተነሳ ለከባድ ረሃብ የተጋለጡ ዜጎቿን ለመታደግ የዝሆን ስጋን ልትመግብ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
የሀገሪቱ የዱር እንስሳት ባለስልጣን በአጣዳፊ ረሃብ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ህይወት ለመታደግ በመላ ሀገሪቱ 200 የሚደርሱ ዝሆኖች ለእርድ ይቀርባሉ ብሏል፡፡
በደቡብ አፍሪካ ሀገራት የኤልኒኖ የአየር ንብረት ተጽዕኖ ባስከተለው ድርቅ 68 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች የምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው ተገልጿል።
የዚምባቡዌ የፓርክ እና ዱር እንስሳት ባለስልጣን ቃል አቀባይ ቲናሺ ፋራዎ በቅርቡ ዝሆኖችን ለማደን አዳኞች እንደሚንቀሳቀሱ እና ስጋው አስከፊ ረሃብ በሚገኝባቸው አካባቢዎች እንደሚከፋፈል ለሮይተርስ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ሀገሪቱ ባሏት ፓርኮች ማስተናገድ የምትችለው 55 ሺህ ዞኖችን ብቻ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የሚገኙት ግን ከ84 ሺህ በላይ እንደሆኑ የገለጹት ቃል አቀባዩ ሂደቱ የዝሆኖችን ቁጥር ከአካባቢ ሁኔታ ጋር ለማመጣጠን ይረዳል ብለዋል፡፡
የዱር እንስሳት ባለስልጣኑ የተፈጥሮ ሀብቶች እጥረት በተፈጠረ ጊዜ በሰው እና እንስሳት መካከል የሚፈጠረው ግጭት እየተባባሰ እንደሚሄድ በመጥቀስ፤ ባሳለፍነው አመት በድርቁ ምክንያት ወደ ሰዎች መንደር የገቡ ዝሆኖች 50 ሰዎችን መግደላቸውን ለማሳያነት አንስቷል፡፡
ከ1988 በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ይደረጋል በተባለው ዝሆኖችን ለምግብነት የማዋል ሂደት አራት ከፍተኛ የዝሆን ቁጥር ይገኝባቸዋል የተባሉ ወረዳዎች ተለይተዋል፡፡
ባሳለፍነው ወር የሃራሬ ጎረቤት የሆነችው ሌላኛዋ ደቡብ አፍሪካዊት ሀገር ናሚቢያ በተመሳሳይ የ83 ዝሆኖችን ስጋ ለድርቅ ለተጎዱ ዜጎች እንዲከፋፈል አድርጋለች፡፡
በዛምቢያ ፣ ዚምባቡዌ ፣ ቦትስወና ፣ አንጎላ እና ናሚቢያን በመሳሳሉ የደቡብ አፍሪካ ሀገራት በሚገኙ ጥብቅ ደኖች ውስጥ ከ200 ሺ በላይ ዝሆኖች እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡
በዚህም ቀጠናው በአለም ላይ በርካታ ዝሆኖች ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ ያደርገዋል፡፡