በፈንሳይ እጅ የነበሩ ወታደራዊ ሰፈሮችንም የአይቮሪኮስት ወታሮች ተረክበው ይቆጣጠሩታል
ምእራብ አፍሪካዊቷ ሀገር አይቮሪኮስት የፈረንሳይ ወታሮች ሀገሪቱን ለቀው እንደሚወጡ መጠየቋን አስታውቃለች።
አይቮሪኮስት ፕሬዝዳንት አላሳን ኦታራ የ2025 አዲስ ዓመትን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር ነው የፈረንሳይ ወታሮች አይቮሪኮስትን ለቀው እንደሚወጡ ያስታወቁት።
የፈረንሳይ ወታደሮችን የማስወጣቱ ሂደት የአይቮሪኮስት ጦር ኃይልን የማዘመን አካል ነው ብለዋል ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው።
የፈረንሳይ ወታደሮችን ከአይቮሪኮስት የማስወጣት ሂደት በ2025 ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅም ፕሬዝዳንት አላሳን ኦታራ አስታውቀዋል።
በፈረንሳይ ጦር የሚተዳደረው የፖርት ቡዌት ወታደራዊ ማዘዣን የአይቮሪኮስት ወታደሮች ተረክበው እንደሚያስተዳሩም ፕሬዝዳንቱ አክለዋል።
አይቮሪኮስት ከምእራብ አፍሪካ ሀገራት መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፈረንሳይ ወታደሮች የሚገኝባት ስትሆን፤ አሁን ላይ በሀገሪቱ ከ600 በላይ የፈረንሳይ ወታሮች በሀገሪቱ ይገኛሉ።
በተመሳሳይ 350 የፈረንሳይ ወታሮች የሚገኙባት ምእራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ሴኔጋልም ባሳለፍነው ወር የፈረንሳይ ጦር ሀገሪቱን ለቆ እንዲወጣ ማዘዟ ይታወሳል።
በፈረንጆቹ በ1960ዎቹ በምዕራብ አፍሪካ የቅኝ ግዛቷ ያበቃው ፈረንሳይ ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ዓመት ወታሮቿን ከማሊ፣ ቡርኪናፋሶ እና ኒጀር ማስወጣቷ ይታወሳል።
ፈረንሳይ ወታሮቿን ከሀገራቱ ለማስወጣት የተገደደችው በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት እና ፀረ ፈረንሣይ አስተያየቶች አመለካከቶች እያደጉ መምጣቱን ተከትሎ ነው።
ከምእራባውያን ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላው የቻድ መንግስትም ባሳለፍነው ህዳር ወር ላይ ከፈረንሳይ ጋር ያለውን ወታራዊ ትብብር ማጠናቀቁን አስታውቋል።
ፈረንሳይ አሁን ላይ ጋቦን እና በጂቡቲ ውስጥ ብቻ ከ2 ሺህ ያነሰ የጦር ሰራዊት እንደሚኖራትም ተነግሯል።