ለበርካታ ዓመታት በቡርኪና ፋሶ የቆየው የፈረንሳይ ጦር አሸባሪዎችን አልተዋጋም በሚል ቅሬታ ቀርቦበታል
የፈረንሳይን ጦር ያባረረችው ቡርኪና ፋሶ የሩሲያውን ዋግነር ቡድን ተቀበለች።
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ቡርኪና ፋሶ ለሩሲያው ዋግነር ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ጥሪ አቅርባለች። ቡርኪና ፋሶ በምዕራብ አፍሪካ ሰፍሮ የነበረው የፈረንሳይ ጦር ሀገሯን ለቆ እንዲወጣ መጠየቋ ይታወሳል።
በፈረንሳይ አስተባባሪነት የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ጦራቸውን በማዋጣት ቡርኪና ፋሶን ጨምሮ በሌሎች ሀገራት ሰፍሮ ነበር።
ይህ የአውሮፓ ጦር ወደ ምዕራብ አፍሪካ ያቀናው በአካባቢው ጽንፈኝነት ተስፋፍቷል፣ ለአውሮፓም ስጋት ነው በሚል ነበር።
ይሁንና ይህ የአውሮፓ ሀገራት ጦር ያሰበውን ያህል ሰላም ማስፈን ባለመቻሉ ምክንያት ትችት ቀርቦበታል።
ጦሩ ከሰፈረባቸው ሀገራት መካከል እንዷ የሆነችው ማሊ የአውሮፓ ጦር ሀገሯን ለቀው እንዲወጡ አድርጋለች።
አሁን ደግሞ ቡርኪና ፋሶ የፈረንሳይን ጦር ከሀገሯ በማስወጣት ለሩሲያው ዋግነር ቅጥረኛ ወታደሮች ቡድን ጥሪ አቅርባለች።
ዋግነር ቡድን በማዕከላዊ አፍሪካ እና ማሊ ተሰማርቶ አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን አድርጓል መባሉን ተከትሎ አሁን ደግሞ ከቡርኪናፋሶ ጥሪ እንደቀረበለት አርቲ ዘግቧል።
ይሁንና ወደ ዩክሬን አቅንቶ እየተዋጋ ያለው ዋግነር ቡድን እስካሁን ከቡርኪና ፋሶ መንግሥት ስለ ቀረበለት ጥያቄ ስለ መቀበሉ እና አለመቀበሉ አስተያየት አልሰጠም።