ቡርኪና ፋሶ የፈረንሳይ ወታደሮች በአንድ ወር ውስጥ ለቀው እንዲወጡ ጠየቀች
ፈረንሣይ ወታደሮቿን ከቡርኪና ፋሶ ለማውጣት አንድ ወር ቀነ ገደብ ተሰጥቷታል
ባለፈው አርብ በፓሪስ ላይ ፀረ-ፈረንሳይ መፈክሮችን ያሰማና ጦሩ ሀገሪቱን ለቆ እንዲወጣ የሚጠይቅ ሰልፍ ተካሂዷል
ቡርኪና ፋሶ የፈረንሳይ ወታደሮች በአንድ ወር ውስጥ ለቀው እንዲወጡ ጠየቀች።
የቡርኪና ፋሶ ወታደራዊ መንግስት በሀገሪቱ የሰፈሩት የፈረንሳይ ወታደሮች ለቀው እንዲወጡ ጠይቋል።
ለቡርኪና ፋሶ ወታደራዊ መንግስት ቅርብ የሆነ ምንጭ የፈረንሳይ ወታደሮች ለቀው እንዲወጡ ጥያቄ መቅረቡን አረጋግጠዋል።
ነገር ግን ምንም ተጨማሪ ዝርዝር አለማግኘቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
የቡርኪና ፋሶ መንግስት የዜና ወኪል እንደዘገበው ወታደራዊው መንግስት በፈረንጆች ጥር18 2018 የተደረሰውንና የፈረንሣይ ወታደሮች በሀገሪቱ እንዲገኙ የሚያስችለውን ወታደራዊ ስምምነት አግዷል።
ፈረንሣይ ወታደሮቿን ከቡርኪና ፋሶ ለማውጣት አንድ ወር እንዳላት አክሎ ገልጿል።
ውሳኔው እ.አ.አ በመስከረም 2022 ከተካሄደው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት በኋላ በፈረንሳይ እና በቀድሞ ቅኝ ግዛቷ መካከል ያለው ግንኙነት የበለጠ መሻከርን የሚያሳይ ነው ተብሏል።
ውጥረቱ የፈረንሳይ ጦር ቡርኪናፋሶ ውስጥ መግባቱ በአማፅያን በታመሰችው ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር የፀጥታ ለውጥ አላመጣም ከሚል ግንዛቤ የመጣ እንደሆነ ተገልጿል።
ባለፈው አርብ በዋና ከተማዋ ዋጋዱጉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች በፓሪስ ላይ ፀረ-ፈረንሳይ መፈክሮችን በማሰማትና የፈረንሣይ ጦር ሀገሪቱን ለቆ እንዲወጣ የሚጠይቁ ምልክቶችን በመያዝ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።
የፈረንሳይ መንግስት ቃል አቀባይ ለጊዜው አስተያየት ሊሰጥ አልቻለም።
ፈረንሣይ 400 የሚያህሉ ልዩ ኃይሎች በሀገሪቱ ውስጥ ያሏት ሲሆን፤ በቀጣናው ከማሊ ጀምሮ ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ በሳሄል አካባቢ የተስፋፋውን እስላማዊ አማፅያን ለመዋጋት የተሰማሩ ናቸው።