ጃፓን በአሜሪካ ብዙ መዋዕለ-ንዋይ ካፈሰሱ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ቀዳሚ ሆነች
ቻይና ለዓመታት በአሜሪካ የግምጃ ቤት ቦንድ ትልቅ ባለሀብት የነበረች ቢሆንም ጃፓን በፈረንጆቹ 2019 የበላይነቱን ወስዳለች
የባህረ ሰላጤው የትብብር ም/ቤት ሀገራት የቀጣናቸው ከፍተኛ በአሜሪካ ባለሀብት መሆናቸው ተነግሯል
ጃፓን በዓለም አቀፍ ደረጃ በቦንድ ግዥና በአሜሪካ የግምጃ ቤት ሂሳቦች "ዕዳ" በመያዝ ደረጃዋን አስጠብቃለች።
በአሜሪካ የግምጃ ቤት ሂሳቦች እና ቦንዶች ላይ የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንቶች በፈረንጆቹ ጥቅምት 2022 መጨረሻ በአንድ ነጥብ አምስት በመቶ መቀነሱ ተነግሯል።
በመስከረም 2022 ከነበረው 7 ነጥብ 297 ትሪሊዮን ዶላር የአሜሪካን የግምጃ ቤት ሂሳቦች እና ቦንዶች ላይ የተደረገው ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንቶች ወደ 7 ነጥብ 185 ትሪሊዮን ዶላር ቀንሳል ነው የተባለው።
የአሜሪካ የግምጃ ቤት ይፋ እንዳደረገው በግምጃ ቤት ሂሳቦች እና በአሜሪካ ቦንዶች ላይ ኢንቨስት ከሚያደርጉ ትላልቅ ሀገራት ጃፓን በ1,078 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ዶላር ቀዳሚ ስትሆን ቻይና ደግሞ በ909 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ቻይና ለዓመታት በአሜሪካ የግምጃ ቤት ቦንድ ውስጥ ትልቅ ባለሀብት መሆኗ ትኩረት ስቦ ቢቆይም ጃፓን በፈረንጆቹ 2019 የበላይነቱን ወስዳለች።
ይህ የሆነው በዩናይትድ ስቴትስ እና በቻይና መካከል ባለው የምጣኔ ሀብት ግንኙነት ላይ ጥላ በጣለው የንግድ ጦርነት ምክንያት ነው ተብሏል።
በሦስተኛ ደረጃ ዩናይትድ ኪንግደም 638 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት በማድረግ የምትከተል ሲሆን፣ ቤልጂየም ደግሞ በ327 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር አራተኛ ደረጃን ይዛለች።
በአሜሪካ ቦንድ እና የግምጃ ቤት ሂሳቦች ውስጥ ትልቁ የባህረ ሰላጤ ባለሀብቶች፤ የባህረ ሰላጤው የትብብር ም/ቤት ሀገራት መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፤ ይህም የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ኢንቨስትመንት በ 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በማደጉ ነው ተብሏል።
የባህረ ሰላጤው ሀገራት ትልቁን ድርሻ የያዘችው ሳዑዲ አረቢያ ስትሆን፤ 121 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት አድርጋለች።
ከባህረ ሰላጤው ሀገራት ኩዌት፣ ኦማን፣ ኳታርና ባህሬን በመከታተል ደረጃውን ይዘዋል።