ጃፓን መከላከያ ሰራዊቷ ሀገሪቱን ከአደጋ የመጠበቅ አቅም እንደሌለው ገለጸች
ሀገሪቱ ዓመታዊ የመከላከያ በጀቷን ወደ 294 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግ ማቀዷን አስታውቃለች
ጃፓን ሰሜን ኮሪያን ጨምሮ ቻይና እና ሩሲያ የደህንነት ስጋት ናቸው ስትል ፈርጃለች
ጃፓን መከላከያ ሰራዊቷ ሀገሪቱን ከአደጋ የመጠበቅ አቅም እንደሌለው ገለጸች፡፡
የእስያዊቷ ጃፓን መከላከያ አዛዥ ጀነራል ሺሂንዴ ዮሺዳ እንዳሉት አሁን ያለው የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ጃፓንን ከየትኛውም አደጋ መጠበቅ በሚችልበት ቁመና ላይ አይደለም ብለዋል፡፡
አዛዡ አክለውም አሁን ያለንበት ወታደራዊ አቋም ጃፓን መጠበቅ የሚያስችል አይደለም ያሉ ሲሆን ከዚህ አደጋ ለመውጣት የአጭር እና የረጅም ጊዜ እቅድ ማውጣት እና መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ጃፓን ከሰሜን ኮሪያ እና ሌሎች ሀገራት ሊደርስባት የሚችለውን ጥቃት ለመመከት የአሜሪካ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን መጠቀም አልያም በአሜሪካ ጦር መሳሪያዎች መጠበቅን እንደ ጊዜያዊ መፍትሄ መወሰዱን አዛዡ ተናግረዋል፡፡
ጃፓንን በዘላቂነት ከየትኛውም ጥቃት ለመመከት ግን ዓመታዊ የመከላከያ በጀትን ማሳደግ ዋነኛ መፍትሔ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጃፓን አሁን ላይ ዓመታዊ የመከላከያ በጀቷ 187 ቢሊዮን ዶላር ነው የተባለ ሲሆን በጀቱን በእጥፍ በማሳደግ ወደ 294 ቢሊዮን ዶላር ከፍ እንዲል መወሰኗን ተገልጿል፡፡
ጃፓን ከወራት በፊት ባወጣችው ብሔራዊ የደህንነት ስጋት ጥናቷ ሰሜን ኮሪያ፣ ቻይና እና ሩሲያ ለጃፓን እና እስያ የደህንነት ስጋት ምንጭ መሆናቸውን ገልጻለች፡፡
ይህን ተከትሎም ከሁለት ሳምንት በፊት አሜሪካ፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ የኔቶ ጥምረትን የሚመስል ወታደራዊ ትብብር መፍጠራቸው ተገልጿል፡፡