ሀገራት ከጃፓን የታዳሽ ሃይል ልማት ምን ይማራሉ?
ቶኪዮ ከጠቅላላ የኤሌክትሪክ ምርቷ 20 በመቶውን ከታዳሽ ሃይል፤ 7 ከመቶውን ደግሞ ከኒዩክሌር ታገኛለች
የጃፓን የታዳሽ ሃይል አቅርቦት በ10 አመት ውስጥ በ174 በመቶ እድገት ማሳየቱ ተገልጿል
የሩቅ ምስራቋ ጃፓን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመግታት አበረታች ስራ እየከወኑ ከሚገኙ ሀገራት ተርታ ትሰለፋለች።
ጃፓን እንደ አረብ ኤምሬትስ ሁሉ በታዳሽ እና ንጹሃ የሃይል ምንጭ እንዲሁም ከነዳጅ ጥገኝነት የተላቀቀ ኢኮኖሚ በመገንባት ላይ ትገኛለች።
የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት በካይ ከሆኑ የሃይል ምንጮች እንዲወጡም “ጃፓን ክላይሜት” የሚል የትብብር ማዕቀፍ አውጥታ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች ከአምስት አመት በላይ ሆኗታል።
በዚህ ማዕቀፍ ውስጥም ከ700 በላይ ተቋማት አባል ሆነው በ2030 ከሚጠቀሙት የኤሌክትሪክ ሃይል ውስጥ ከ35 በመቶ በላዩ ከታዳሽ ሃይል ምንጮች እንዲሆን ስራዎች ቀጥለዋል ነው የተባለው።
በ2050 ሙሉ በሙሉ ካርበን የማይበክላት ቶኪዮን እውን ለማድረግ የተቀመጡ ግቦችን እውን ለማድረግ የተወሰዱት እርምጃዎችም ከወዲሁ ውጤት እያሳዩዋት ነው።
የሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው በ2021 ከጠቅላላ የጃፓን የኤሌክትሪክ ሃይል ምርት የታዳሽ ሃይል ምንጮች ድርሻ 20 በመቶ ደርሷል።
ቶኪዮ ከኒዩክሌር የምታገኘው ሃይልም የ7 ከመቶ ገደማ ድርሻ እንዳለው ነው የተጠቀሰው።
ሀገሪቱ የ2020 የታዳሽ አቅርቦቷ በ2011 ከነበረበት በ171 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱም ተገልጿል።
ከ2025 ጀምሮ በእያንዳንዱ ኩባንያ እና የግለሰብ መኖሪያ ቤት ጣሪያ ላይ የጸሃይ ሃይል ማመንጫ (ሶላር ፓኔል) እንዲሰቀል ማድረግ እንደምትጀምርም ነው የሀገሪቱ መንግስት እቅድ የያዘው።
የጃፓን የኢኮኖሚ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው ሀገሪቱ እስከ 2030 ባሉት አመታት የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ እስከ 132 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ፕሮጀክቶችን ትጀምራለች።
በፈጣን እድገት ላይ ያለችው ሀገር ኤምሬትስ በህዳር ወር በምታዘጋጀው የአለማቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የእስካሁን ስኬቷን ታጋራለች ተብሎ ይጠበቃል።