የጃፓን- አፍሪካ ጉባኤ በቱኒዝያ ተካሂዷል
ጃፓን ለአፍሪካ 30 ቢሊዮን ዶላር እንደምትለግስ አስታውቃለች።
የአፍሪካ- ጃፓን ጉባኤ በቱኒዝያ መዲና ቱኒዝ ላለፉት ሁለት ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል።
በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተው በአካል ወደ ቱኒዝ መጓዝ ያልቻሉት የጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ፉሚዮ ኪሺዳ በበይነ መረብ ታግዘው ባደረጉት ንግግር ጃፓን ለአፍሪካ 30 ቢሊዮን ዶላር ትሰጣለች ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለውም በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት አፍሪካ አንዷ ተጎጂ መሆኗን ጠቅሰው አፍሪካ በምግብ እጥረት እንዳትጎዳ ድጋፍ ታደርጋለችም ብለዋል።
ዓለም በስርዓት እንድትመራ ሁላችንም መጣር አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ አፍሪካ በሀይል የሚደረጉ ነገሮችን ሁሉ ከተቀረው ዓለም ጋር እንድትታገል ጥሪ አቅርበዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ጃፓን ለአፍሪካ ለመለገስ ቃል የገባችው 30 ቢሊዮን ዶላር በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ እንደምትፈጽምም ጠቅላይ ሚንስትሩ ጠቁመዋል።
የሩቅ ምስራቋ ሀገር ጃፓን የቻይናን በአፍሪካ ተጽዕኖ ለመቋቋም ከአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት ከሚመራው የምዕራባውያን ሀገራት ጎራ ጎን ትገኛለች።
የምስራቁን ጎራ መሪ የሆነችው ቻይና ከጃፓን ጋር ያላት ግንኙነት እየተሸተሸረ የመጣ ሲሆን የዩክሬን እና ታይዋን ጉዳይ ደግሞ ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሻከር ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው።