በአሜሪካ ጽንስ የማቋረጥ ሕገ መንግሥታዊ መብት ተሻረ
የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍ/ቤት የጽንስ ማቋረጥን ጉዳይ ለየግዛቶቹ ሰጥቷል
ጽንስ የማቋረጥ ውሳኔን ከወሰነ በኋላ በርካቶች ድጋፍም ተቃውሞም እያሰሙ ነው
በአሜሪካ ላለፉት ዓመታት ሕገ መንግሥታዊ ሆኖ የቆየው የጽንስ ማቋረጥ መብት መሻሩ አነጋጋሪ ሆኗል።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ1973 የወጣውን ሮ ቪ ዌድ ተብሎ የሚጠራውን ውሳኔ በዛሬው ዕለት መሻሩን አስታውቋል። ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ሲሰራበት የቆየውና በሕገ መንግስት ጭምር የሰፈረው ይህ የጽንስ ማቋረጥ መብት ተሽሯል።
ከዚህ በኋላ በአሜሪካ ጽንስን ማቋረጥን የመፍቀድም ሆነ የመከልከል ስልጣን ለግዛቶቹ መሰጠቱን ነው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የገለጸው።
በዚህ መሰረት ጽንስን የማቋረጥ ጉዳይ በፌዴራል የሚታይ ሳይሆን እንደየግዛቶቹ ሁኔታ የሚወሰን ይሆናል ነው የተባለው።
በአሜሪካ ጽንስ ማቋረጥን የሚፈቅዱትም ሆኑ የሚከለክሉት ግዛቶች መሆናቸውን ተከትሎ አንዳንዶቹ እንደማይፈቅዱ እየገለጹ ነው።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይህንን ውሳኔ መወሰኑን ተከትሎ በአሜሪካና ከአሜሪካ ውጭ ባሉ ሀገራት ውስጥ ያሉ የመብት ተሟጋቾች ተቃውሞ እያሰሙ ናቸው።
የቀድሞው የአመሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሚሊዮኖችን መሰረታዊ ነጻነትን ዝቅ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የቀድሞው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ በበኩላቸው ጽንስ ማቋረጥ በሁሉም ግዛቶች መከልከል እንዳለበት አሳስበዋል።