ጃፓን የፉክሺማ ጣቢያን የኒዉክሌር ውሃ ወደ ውቅያኖስ ልትለቅ ነው
እርምጃው ከቻይናና ከአሣ አጥማጆች ከፍተኛ ትችት ገጥሞታል

ጃፓን የውሃው ደህንነት እንደማያሰጋ ተናግራለች
ጃፓን ከአንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ "የታከመ" 'ራዲዮአክቲቭ' ውሃ ከተበላሸው የፉኩሺማ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ መልቀቅ እንደምትጀምር አስታውቃለች።
በቶኪዮ ኤሌክትሪክ ኃይል ኩባንያ የሚተዳደረው ጣቢያ ስራ ለማቆም ከሁለት ዓመት በፊት ያወጣው እቅድ በጃፓን መንግስት ጸድቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ባለስልጣን በፈቀደው እቅድ መሰረት ውሃው እንዲለቀቅ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል።
ውሃው ከሀሙስ ጀምሮ መለቀቅ እንደሚጀምርም ገልጸዋል።
እርምጃው ከቻይና ከፍተኛ ትችት ገጥሞታል።
እቅዱ ከአካባቢው የአሳ አጥማጆች ቡድንም ወቀሳ ገጥሞታል።
ይህ የተባለው የጃፓን መንግስት ከውሃው መለቀቅ ጋር በተያያዘ ከዓሳ አጥማጆች ጋር "በተወሰነ ደረጃ መረዳት አግኝቻለሁ" ካለ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
ምንም እንኳን የአሳ አጥማጆች ቡድን አሁንም እርምጃው ኑሯችንን ይጎዳል በሚል ስጋት ላይ ናቸው።
ጃፓን የውሃው ደህንነት እንደማያሰጋ ተናግራለች።
የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይለሰ ኤጀንሲ እና የተመድ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ድርጅት እቅዱን ፈቅደዋል።