ጃፓን "ቆሻሻ የመሰብሰብ" የአለም ዋንጫ ውድድርን ልታዘጋጅ ነው
ከሶስት እስከ አምስት ሰዎች የሚሳተፉበት ውድድር እያዝናና የከተማን ውበት ያስጠብቃል ተብሏል
ጃፓናውያን በቅርቡ በኳታር በተካሄደው የአለም ዋንጫ በስታዲየሞች ቆሻሻ ሲሰበስቡ ታይተዋል
ጃፓን የመጀመሪያውን "የቆሻሻ መሰብሰብ" የአለም ዋንጫ ልታስተናግድ ነው።
በህዳር ወር 2023 በሚደረገው ውድድር ሀገራት ከ3 እስከ 5 ተወካዬቻቸውን ይለካሉ።
ተወዳዳሪዎቹ በቶኪዬ ጎዳናዎች የተጣሉ ልዩ ልዩ ቆሻሻዎችን በፍጥነት በመልቀም ይሳለፋሉ ነው የተባለው።
ሶስት አባላት የሚኖሯቸው ቡድኖች ለ60 ደቂቃዎች የተለያየ የቀለም ኮድ የተሰጣቸውን የቆሻሻ አይነቶች በተዘጋጀላቸው የፕላስቲክ ማጠራቀሚያ ይከታሉ።
ከዚያም የሰበሰቡትን ቆሻሻ የሚያስመዝኑ ሲሆን፥ ከባድ ቆሻሻ የሰበሰበው ቡድን አሸናፊ ይሆናል።
ተመሳሳይ ክብደት ያለው ቆሻሻ የሰበሰቡትም በቆሻሻው አይነት (እጅግ በካይ ቆሻሻ የሰበሰበ) እኝደሚወሰንም ነው የውድድሩ አዘጋጅ ታካያሱ ኡዳጋዋ።
ኡዳጋዋ በዚህ ውድድር ስንት ሀገራት እንደሚሳተፉና ምን አይነት ሽልማት እንደተዘጋጀ ግን አልገለፁም።
ስፓርትን ከንፅህና ያዋሃደው የአለም ዋንጫ አውራ ጎዳናዎችና የህዝብ መገልገያ ስፍራዎችን ንፅህና ለመጠበቅ ያግዛል ተብሏል።
ከውድድር አንፃር ግን አሸናፊውን ለመለየት አስቸጋሪ እንደሚሆን ነው የሚጠበቀው።
ጃፓናውያን በፈረንጆቹ 1998 በፈረንሳይ ካደረጉት የመጀመሪያ የአለም ዋንጫ ተሳትፏቸው ጀምሮ ለቆሻሻ አወጋገድ የሰጡትን ትኩረት ለአለም አሳይተዋል።
በቅርቡ በኳታር በተካሄደው የአለም ዋንጫም የጃፓን ደጋፊዎች በስታዲየሞች ቆሻሻ ሲሰበስቡ ታይተዋል።
በሀገር ቤት በፈረንጆቹ 2008 የጀመረችው ቆሻሻን የመሰብሰብ ውድድርም ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።