ባለጸጋው ኤለን መስክ ለበጎ አድራጎት ተቋማት 2 ቢሊየን ዶላር መለገሱን ገለጸ
የአለማችን ሁለተኛው ባለጠጋ በዱባይ በተካሄደው የአለም የመንግስታት ጉባኤ በቪዲዮ መልዕክት አስተላልፏል
መስክ በ44 ቢሊየን ዶላር የገዛውን ትዊተር የሚመራ ስራ አስፈጻሚን በዚህ አመት መጨረሻ እንደሚሾም ገልጿል
ኤለን መስክ ለበጎ አድራጎት ተቋማት 2 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ የቴስላ አክሲዮኖችን መለገሱን አስታውቋል።
መስክ ትናንት በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በተጀመረው የአለም የመንግስታት ጉባኤ በቪዲዮ ባስተላለፈው መልዕክት ላይ ነው ይህን የገለጸው።
የአለማችን ሁለተኛው ባለጠጋ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራቹን ቴስላ 11 ነጥብ 6 ሚሊየን አክሲዮኖች ለረድኤት ተቋማት መለገሱን ይፋ አድርጓል።
የትኞቹ ተቋማት ተጠቃሚ እንደሆኑ ግን በንግግሩ ላይ አልጠቀሰም።
ቴስላም 1 ነጥብ 95 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣውን የአክሲዮን ልገሳ በተመለከተ ዝርዝር መረጃን አልሰጠም ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
መስክ በ2021ም 5 ነጥብ 74 ቢሊየንድ ዶላር የሚያወጡ አክሲዮኖችን መለገሱን ዘገባው አስታውሷል።
በዱባይ በተካሄደው የአለም የመንግስታት ጉባኤ ባለጸጋው ሌላው ያነሳው ጉዳይ በ44 ቢሊየን ዶላር ስለገዛው የማህበራዊ ትስስር ገጽ ትዊተር ነው።
ትዊተርን በስራ አስፈጻሚነት እየመራ ያለው መስክ በዚህ አመት መጨረሻ የሚተካውን ሰው ይፋ እንደሚያደርግ ነው ያስታወቀው።
ኪሳራ ውስጥ የነበረውን ትዊተር ወደ ትርፋማነት ለመመለስና ጠንካራ መሰረት እንዲኖረው ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑንም አንስቷል።መስክ ትዊተርን ከገዛ በኋላ ሙሉ ትኩረቱን ነፍጎናል በሚል በቴስላ ባለአክሲዮኖች ተደጋጋሚ ወቀሳ ይቀርብበታል።
ባለጸጋው በትዊተር ገጹ ላይ ኩባንያው አዲስ ስራ አስፈጻሚ ይሾምለት ወይ? የሚል መጠይቅ አቅርቦ አብላጫው አዲስ ስራ አስፈጻሚ እንዲሾም መጠየቁ የሚታወስ ነው።
የስፔስ ኤክስ፣ ቴስላ እና ትዊተር ባለቤቱ ኤለን መስክ የስራ ጫና እንደበዛበት በኢንዶኔዥያ ባሊ በተካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት ስብሰባ ላይ መናገሩም አይዘነጋም።
A