የ2 የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች የምጣኔሃብት ጉዳዮች አማካሪ የነበሩት አቶ ንዋይ ማናቸው?
የኢትዮጵያ መንግስት የምጣኔ ሃብት አማካሪ ሆነው ለረጅም ዓመታት ያገለገሉት አቶ ንዋይ ገብረዓብ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ተሰምቷል፡፡
አቶ ንዋይ የቀድሞ ሁለት ጠቅላይ ሚኒስትሮች የምጣኔ ሃብት ጉዳዮች አማካሪ ነበሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን እና ኃይለማርያም ደሳለኝን ስለማማከራቸውም ይነገራል፡፡
ለመሆኑ እኝህ ከሁለት አስርት አመታት በላይ መንግስትን ያማከሩት ንዋይ ገብረዓብ ማናቸው?
አቶ ንዋይ ከ1960ዎቹ እና ከ1970ዎቹ መባቻ ጀምሮ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና በፕላን ኮሚሽን ውስጥም ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች አማካሪ ሆነውም በዩናይትድ ኪንግደም ሰርተዋል።
ኢህአዴግ ሃገሪቱን በተቆጣጠረበት በ1983 ዓ/ም ወደ ሃገራቸው በመመለስም በተለያዩ የአማካሪነት ቦታዎች ላይ አገልግለዋል፡፡
ከሃገሪቱ መሪዎች ምጣኔሃብታዊ ጉዳዮች አማካሪነት ባለፈም ከ1990ዎቹ መባቻ ጀምሮ የኢትዮጵያ የልማት ጥናት ኢንስቲትዩትን በዋና ዳይሬክተርነት መርተዋል።
አቶ ንዋይ ከቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ (ከአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ) የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል።
አቶ ንዋይ በድርቅና በተለያዩ ችግሮች የሚፈተነው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት እና የዜጎች ህይወት እንዲሻሻል ለማድረግ እንደሚያስችሉ የታመነባቸውን የመንግስት የቤት ስራዎች በማማከር ይታወቃሉ፡፡
በተለይ ግብርና መሩ ምጣኔ ሃብት መዋቅራዊ ሽግግርን እንዲያደርግና በዝቅተኛነት ይጠቀስ የነበረው የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ90 ዶላር ከፍ እንዲል በማማከር ረገድ የጎላ ሚናን ተጫውተዋል፡፡
በአቶ መለስ የተጀመረውን አረንጓዴ ምጣኔ ሃብትን የመገንባት ስትራቴጂ በማማከርም ይታወቃሉ፡፡ይህንኑ የቤት ስራ እንዲያስተባብሩም ቀደም ባሉት ጥቂት አመታት ኃላፊነት ተሰጥቷቸው አገልግለዋል፡፡
አቶ ንዋይ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራት የሚያደርጉ ኢኮኖሚያዊ ስምምነቶችን እና ሌሎች አገራዊ ጉዳዮችን ሲያማክሩም ቆይተዋል።
ይህንኑ አበርክቷቸውን ታሳቢ በማድረግም መንግስት በ2009 ዓ/ም የአፍሪካ ህብረት የኢኮኖሚ ኮሚሽንን በኮሚሽነርነት እንዲመሩ እጩ አድርጎ አቅርቧቸው ነበር፡፡ ይህ የሆነው ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የዓለም የጤና ድርጅትን እንዲመሩ በተመረጡ ጥቂት ወራት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ሆኖም ውጥኑ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
የካይዘን ፍልስፍና በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ በማድረግ ረገድም ትልቅ አበርክቶ ነበራቸው ነው የሚባለው፡፡ ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ ሽልማትንም በ2008 ዓ/ም ከጃፓን መንግስት ተቀብለዋል ፡፡
ሽልማቱ "በወርቅና ብር የተንቆጠቆጠ የንጋት ፀሐይ የክብር ኒሻን" በመባል እንደሚታወቅ ኢዜአ በወቅቱ ዘግቦ ነበር፡፡
ሽልማቱ የኢትዮ-ጃፓን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ መታሰቢያነት የተሰጠ መሆኑን የገለጹት የወቅቱ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ካዙሂሮ ሱዙኪ''አቶ ንዋይ የኢትዮ-ጃፓን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ምክክር ልማት ፎረም መስራች ከመሆናቸውም በላይ በፎረሙ በርካታ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት እንዲቀላቀሉ አግዘዋል'' ማለታቸውንም ነበር በወቅቱ ኢዜአ የዘገበው፡፡
አቶ ነዋይ በ2009 ዓ/ም ጡረታ ወጥተዋል፡፡ የቀድሞው የብሄራዊ ባንክ ገዢ አጥናፉ ተክለወልድ እና የቀድሞው የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ሱፊያን አህመድ እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበትም በሂልተን ሆቴል አሸኛኛት ተደርጎላቸው ነበር፡፡
ሆኖም መንግስትን ለረዥም አመታት ያማከሩት እኚህ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ባደረባቸው ህመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ዛሬ የካቲት 16 ቀን 2012 ጠዋት ማረፋቸውን ነው የትግራይ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ያስታወቀው።