ሰዎቹ ከለውጡ ጋር በተያያዘ በተፈጠሩ ግጭቶች ከታሰሩት መካከል ናቸው
በእስራት ላይ የሚገኙ 60 የመንግስትና የፓርቲ አመራሮች የክስ ሂደት እንዲቋረጥ ተወሰነ
ጉዳያቸው በህግ በመታየት ላይ የነበሩ 60 ሰዎች የክስ ሂደት እንዲቋረጥ መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬስ ሴክረታሪያት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስታውቀዋል፡፡
ከለውጡ ጋር በተያያዘ በተፈጠሩ ግጭቶች ከፍተኛ የህይወትና የንብረት ውድመት ማጋጠሙን ያስታወቁት አቶ ንጉሱ በአጠቃላይ 1ሺ 600 ሰዎች ተጠርጥረው መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡
በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር እና አላግባብ ሲንቀሳቀስ ነበረ የነበረ በአጠቃላይ ግማሽ ቢሊዮን ገደማ ገንዘብ ታግዷልም ብለዋል፡፡
ጉዳያቸው በመታየት ላይ ካሉ ከ1ሺ በላይ ሰዎች መካከል የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እና ሰላማዊ ሁኔታን ለመፍጠር በማሰብ መስረጃዎች ቢኖሩም ትምህርት ተወስዶበት የ60ዎቹ ክስ እንዲቋረጥ መንግስት መወሰኑንም አስታውቀዋል፡፡
ሆኖም ክስ የማቋረጡ ዝርዝር እንደ ህጉ አግባብ በምን ጉዳዮች ላይ እነማን ናቸው የሚለውን ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እንደሚያስታውቅም ነው አቶ ንጉሱ የተናገሩት፡፡
በለውጡ ሂደት ከተለቀቁ 43 ሺ 530 ሰዎች አብዛኛዎቹ ሰላማዊ ኑሮን እየመሩ እንደሚገኙም አስታውቀዋል፡፡
በቅርቡ ከትግራይ የብልጽግና ፓርቲ አመራር አባላት ጋር የመከሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ክሳቸው ተቋርጦ የሚፈቱ ሰዎች እንደሚኖሩ ፍንጭ መስጠታቸው የሚታወስ ነው፡፡