ጃፓን በ2030 ዓመታዊ የጎብኚዎችን ቁጥር ወደ 60 ሚሊዮን የማሳደግ እቅድ ነድፋለች
የሩቅ ምስራቋ ጃፓን በተጠናቀቀው የ2024 ዓመት የጎበኟት የውጭ ዜጎች ቁጥር 37 ሚሊዮን ገደማ ደርሷል፡፡
ሀገሪቱ በ2019 ላይ በ32 ሚሊዮን ጎብኚዎች የተጎበኘች ሲሆን ይህም በታሪክ ትልቁ ቁጥር ሆኖ ተመዝግቦ ነበር፡፡
በ2024 ዓመት ውስጥ በአጠቃላይ በ36 ነጥብ 8 ሚሊዮን ጎብኚዎች መጎብኘቷን ኤኤፍፒ የሀገሪቱ ብሔራዊ ቱሪዝም ድርጅትን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ ጃፓን ጎብኚዎቿ የበዙት የሀገሪቱ መገበያያ ገንዘብ የሆነው የን ከዶላር ጋር ያለውን ልዩነት በማዳከሟ፣ ከፍተኛ የጎብኚዎች ማበረታቻዎችን በመከተሏ እና ጥሩ ማስታወቂያዎችን በመስራቷ ነው ተብሏል፡፡
በ2024 ጃፓንን የጎበኙት የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ከ12 ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በአራት እጥፍ ጨምሯል፡፡
አዲሱ የፈረንጆቹ 2025 ዓመት የገባበት ጥር ወር ዋና የጎብኚዎች መምጫ ወር ሲሆን ጃፓንን ይጎበኛሉ ተብለው ከሚጠበቁት ውስጥ 30 በመቶዎቹ መመዝገባቸው ተገልጿል፡፡
በኪሎ ከ13 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣው የጃፓን ሩዝ
ጎብኚዎች በሚበዛባቸው የተወሰኑ የጃፓን ከተሞች ላይ ነዋሪዎች ጎብኚዎች በዙ የሚሉ ተቃውሞዎችን ያሰማሉ፡፡
የሀገሪቱ መንግስት ይህንን ለመፍታት ያልተለመዱ እና አዳዲስ የጎብኚዎች መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ ማሰቡም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
120 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ጃፓን በዓለም ላይ በብዛት ከሚጎበኙ አምስት ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን በዓመት ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢዋን ከቱሪዝም ዘርፍ ታገኛለች፡፡