የጃፓን ኩባንያ ሰው የሚያጥብ ማሽኑን ሊያስተዋውቅ ነው
የእንቁላል ቅርጽ ያለው ማሽን ሚሊየን እጅግ ደቃቅ አረፋዎችን በመልቀቅ ቆሻሻን በፍጥነት ያጸዳል ተብሏል
ማሽኑ 1 ሺህ ሰዎች ከሞከሩት በኋላ ለገበያ እንደሚቀርብ ተገልጿል
በቴክኖሎጂው ዘርፍ ቀዳሚ ከሆኑት ሀገራት መካከል የምትጠቀሰው ጃፓን ሰዎችን የሚያጥብ ማሽን ሰርታለች።
"ሳይንስ" የተሰኘው የንጽህና መጠበቂያ አምራች ኩባንያ ነው ማሽኑን የሰራው።
ኩባንያው በኦሳካ በቀጣዩ የፈረንጆቹ አመት 2025 በሚካሄደው የቴክኖሎጂ አውደርኦይ ላይ ይቀርባል ብሏል።
የ"ሳይንስ" ፕሬዝዳንት ያሱኬ አያማ የመጀመሪያውን "ሰዎችን ማጠቢያ ማሽን" የተመለከቱት በፈረንጆቹ 1970 ነው። ይህን ማሽን ሰርቶ ለእይታ ያቀረበው "ሳንዮ ኤሌክትሪክ" የተሰኘ ኩባንያ ነው።
አያማ የአራተኛ ክፍል ተማሪ እያለ ማሽኑን ከተመለከተው በኋላ ከአዕምሮው ሊጠፋ እንዳልቻለ ይናገራል። እናም በዚሁ ማሽን ላይ በሚሰራው ኩባንያ ላይ ተቀጥሮ እስከ ፕሬዝዳንትነት ደርሷል።
የ1970ው ማሽን ትልልቅ አረፋዎችን እና "አልትራሶኒክ ዌቭ" በመፍጠር ነው ሰውነትን የሚያጥበው።
በ2025 ይፋ የሚደረገው አዲስ ማሽን ግን እጅግ ደቃቅ አረፋዎችን በመፍጠር ቆሻሻን በፍጥነት ማጽዳት ይችላል ተብሏል።
ማሽኑ ዘመናዊ ሴንሰሮች የተገጠሙለት በመሆኑም ሊታጠቡበት የሚገቡ ሰዎችን የልብ ምት እና የሰውነት ሙቀት በመለካት የውሃ ሙቀቱን ያስተካክላል።
ከዚህም ባሻገር የሰዎችን ወቅታዊ ስሜት (ደስታ ወይም ድብርት) የሚለይ ቴክኖሎጂ ስላለው ተጠቃሚዎቹ በውስጡ እንዳሉ መረጃውን ያጋራቸዋል።
ኩባንያው እስካሁን አዲሱን ሰው የሚያጥብ ማሽን ምስል ባያሳይም እንቁላል መሰል ቅርጽ እንዳለው የጃፓን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በከፊል በሙቅ ውሃ የሚሞላው ማሽን ውስጥ የሚገባው ሰው መሃል ላይ ባለው መቀመጫ ላይ ይቀመጣል። ከዚያም በሚሊየን የሚቆጠሩ ደቃቅ አረፋዎች ተለቀው በፍጥነት ሰውነት ላይ ያሉ ቆሻሻዎችን ያጸዳሉ ተብሏል።
"ሰው የሚያጥበው ማሽን" 1 ሺህ ሰዎች እንዲሞክሩት ከተደረገ በኋላ ለገበያ እንደሚቀርብ ኩባንያው ገልጿል።