ለአምስት አመታት አልጋውን ይዞ የሚዞረው ጃፓናዊ
የ33 አመቱ ወጣት ሲመሻሽ "የእግዜር እንግዳ ነኝ አሳድሩኝ" የሚል ጽሁፍ አንግቶ ህዝብ በተሰበሰበበት አካባቢ ይቆማል

ከ500 በላይ የሚሆኑ ሰዎች የማያውቁትን እንግዳ ተቀብለው እንዳሳደሩት ተናግሯል
ጃፓናዊው ወጣት ባለፉት አምስት አመታት ማደሪያ አልጋውን በአንገቶ ላይ አንግቶ መዞሩ ትኩረት ስቧል።
ሹራፍ ኢሽዳ የተባለው የ33 አመት ወጣት ስራውን ከለቀቀ በኋላ ወሳኝ ከሚላቸው ጥቂት እቃዎች ውጪ ሁሉንም ንብረቱን ሽጦ በመላ ሀገሪቱ እየተንቀሳቀሰ መኖሩን መርጧል።
የሸጠው ንብረትና ያጠራቀመው ገንዘብ ግን ምግብ ቢሸፍን እንጂ ውድ ለሆነው የመኝታ ወጪ እንደማይበቃው ያምናል።
በዚህም አንድ ሃሳብ ይመጣለታል፤ ሰዎች በቤታቸው እንዲያሳድሩኝ ለምን አልጠይቅም የሚል።
ኢሽዳ በየቀኑ "እባካችሁ በናንተ ቤት ልደር" የሚል መልዕክት ያረፈበትን ጽሁፍ አንገቱ ላይ አንግቶ ህዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ ይቆማል።
ይህን ያልተለመደ መልዕክት የሚያነቡ በተለይ ብቸኛ የሆኑ ሰዎችም "የእግዜር እንግዳ" ብለው ወደ ቤታቸው ወስደው ያሳድሩታል።
ባለፉት አምስት አመታት ከ500 በላይ የተለያዩ ቤቶች ውስጥ ማደሩን የሚገልጸው ጃፓናዊ፥ ማደሪያ ሲያጣ ብቻ ቀድመው ቤታቸውን ወደከፈቱለት ሰዎች እንደሚያቀና ተናግሯል።
ከመላመዳቸው የተነሳ አንዳንዶቹ እንደጓደኛቸው እየተመለከቱት ሚስጢራቸውን ጭምር እንደሚነግሩትም ነው ከጃፓኑ ኤፍኤንኤን ጋር በነበረው ቆይታ የገለጸው።
ለረጅም ስአት ቆሞ አሳዳሪ የሚጠብቅበትን ሁኔታ አሳ ከማጥመድ ጋር ያመሳሰለው ኢሽዳ፥ የሚያሳድሩኝ ሰዎችን ታሪክ መስማት እጅግ አስደሳቹ ነገር ነው ብሏል። አልጋ ወይ ሶፋቸውን ለማደሪያ የሚፈቅዱለት ሰዎችን ታሪክ መስማት "በየምሽቱ የተለያዩ ልቦለዶችን እንደማንበብ ነው" ሲልም ተናግሯል።
አይናፋሩ ኢሽዳ በታይዋን ለትምህርት በተጓዘበት ወቅት የተመገበው ጣፋጭ ምግብና ያገኛቸው ሰዎች በሙሉ ጉዞ የማድረግ ፍላጎቱን ጨምሮታል።
ከዩኒቨርሲቲ እንደተመረቀ የተቀጠረበት የጃፓን ኩባንያ "መላው አለምን ለመዞር ገንዘብ ቆጥቡ" የሚል ግብ ማስቀመጡም ይህንኑ ፍላጎቱን አጠናክሮት ስራውን ለቆ ጃፓንን ተዟዙሮ እየጎበኘ ነው።
በአሁኑ ወቅት ያጠራቀመው ገንዘብ እያለቀ ቢሆንም ወደ ስራው የመመለስ ውጥን የለውም። ገንዘቡ እስኪያልቅ ድረስ በልዩ የኑሮ ዘይቤው እንደሚቀጥል ገልጿል።
ጃፓናውያን የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች "ከስራ ይልቅ በሰዎች መልካምነት ጥገኛ ሆኗል" በሚል የ33 አመት ወጣት ድርጊት ሊወገዝ የሚገባው ነው ብለዋል።
በቤታቸው ተቀብለው ያስተናገዱት ሰዎች ግን ገንዘብ ይዞ መገኘት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው በኢሽዳ አይተናል፤ ለአንድ ሌሊትም ቢሆን ብቸኝነታችን አስረስቶናል በሚል ይከላከሉለታል።
ሹራፍ ኢሽዳ የጃፓን መገናኛ ብዙሃንን ቀልብ ከሳበ በኋላም በርካታ ሰዎች እንዲጎበኛቸው እየጋበዙት ነው ተብሏል።