ጃፓን ሰራተኞች ቆመው የሚተኙባቸውን አልጋዎች በምግብ ቤቶች መግጠም ጀመረች
በሀገሪቱ በእንቅልፍ እጦት ምክንያት በየአመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን ያጣሉ
በስራ መሃል አጭር እንቅልፍ መተኛት የስራ ውጤታማነትን ያሳድጋል ተብሎ ይታመናል
እስያዊቷ ሀገር ጃፓን ለረጅም ስአት በስራ የደከሙ ዜጎቿ አጭር እረፍት የሚያደርጉባቸውን አልጋዎች በየምግብ ቤቶቹ እየገጠመች ነው።
ጃፓን ለረጅም ስአት በሚሰሩ ሰራተኞቿ ትታወቃለች።
ይህ ለረጅም ስአት ያለእረፍት የመስራት ባህል ሀገሪቱን ፈጣን እድገት እንድታስመዘግብ ቢያደርጋትም ችግር ማስከተሉ አልቀረም።
ቶኪዮ ከ1970ዎቹ ወዲህ ሀገሬው “ካሮሺ” በሚለው የማህበራዊ ችግር ውስጥ ወድቃለች።
የአለም ጤና ድርጅት ጥናት እንደሚያሳየው በጃፓን በእንቅልፍ ማጣት በየአመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጤናቸው ተቃውሶ ህይወታቸው እያለፈ ነው።
ይህን ችግር ለመፍታት ያለመው ኮዮጁ ፕላይውድ ኮርፖሬሽን የተባለው ኩባንያ ዜጎች ለአጭር ጊዜ የሚተኙባቸውን አልጋዎች በየምግብ ቤቶቹ መግጠም መጀመሩም የእረፍት ማጣት ቀውሱን ያሳያል ተብሏል።
አልጋዎቹ በተለምዷዊው መንገድ ቢሰሩ ቦታ ስለሚይዙ አግድም ሳይሆን ሽቅብ የሚቆሙ ተደርገው ተሰርተዋል።
በአልጋዎቹ የሚተኙት ሰዎች የማንቂያ ደወል (አላርም) ሞልተው በምቾት አጭር እንቅልፍ (ናፕ) ይተኛሉ የሚለው “ጂራፍናፕ” የተባለው መኝታ አቅራቢ ኩባንያ ፥ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን የሚደግፉ መሳሪያዎች እንደተገጠሙላቸው ገልጿል።
አልጋዎቹ ተገልጋዮች እንደየቁመትና ውፍረታቸው ሊያስተካክሏቸው የሚችሉ ናቸውም ብሏል።
ሲተኙ ለስለስ ያለ ሙዚቃ መስማት የሚፈልጉ ካሉም መስማት ይችላሉ ነው የተባለው።
በጃፓን ምግብ ቤቶች ተገጥመው አገልግሎት መስጠት የጀመሩት “ጂራፍናፕ” አልጋዎችን በሌሎች ሰዎች በሚበዙባቸው ስፍራዎች ለመግጠም መታቀዱም ተገልጿል።
ሰዎች ቆመው የሚተኙበት “ጂራፍናፕ” አልጋ ስያሜውን ከረጅሟ ቀጭኔ ጋር አያይዞ አውጥቷል።
ሰራተኞቻቸው ለረጅም ስአት የሚሰሩባቸው እንደ ጎግል ያሉ ኩባንያዎች በቢሮ ውስጥ ሰራተኞች የሚተኙባቸውን አልጋዎች ማዘጋጀታቸው ይታወቃል።
ይህም መነቃቃትን እና የስራ ውጤታማነትን ያሳድጋል ተብሎ ይታመናል።