ለሚስቱ በቀን ከ100 ጊዜ በላይ የሚደውለው ጃፓናዊ በቁጥጥር ስር ዋለ
የ38 አመቱ ወጣት በማይታወቅ ስልክ ቁጥር ከአንድ ወር በላይ ሲደውል ነበር ተብሏል
በጃፓን በስራ ምክንያት የተራራቁ ባለትዳሮች አንዱ የሌላኛውን ስልክ የመጥለፍ ልምድ እንዳለ ይነገራል
በጃፓን በቀን እስከ 100 ጊዜ ሲደውል ነበር የተባለ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ።
በዮጎ ግዛት የአማጋሳኪ ከተማ ነዋሪ የሆነው የ38 አመት ወጣት በማይታወቅ ስልክ ደውሎ ባለቤቱ ካነሳችው በኋላ ምንም ሳይናገር ስልኩን ይዘጋ ነበር ተብሏል።
የ31 አመቷ ባለቤቱ በፈረንጆቹ ሀምሌ ወር መጀመሪያ አንስቶ ከማይታወቅ ስልክ ቁጥር የሚደርሳት ጥሪ ሲረብሻት መቆየቱን ትገልጻለች።
የሚደወልበት ስልክ ቁጥር የማይታወቅ (አኖኒመስ) በመሆኑ በድጋሚ እንዳይደውል (ብሎክ) ለማድረግ ባለመቻሏም ከአንድ ወር በላይ ጥሪው መቀጠሉንም ነው የተናገረችው።
ምሽት ላይ እና በባለቤቷ ስልክ ጌም ስትጫወት ግን ያልተለመደው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ይቆማል።
እንስቷ በሀምሌ ወር የጀመረው የስልክ ጥሪ በነሃሴም ሲቀጥልና ከባሏ ጋር ስትተኛ የመቆሙ ነገር ጥርጣሬዋን በባሏ ላይ አድርጋ ለፖሊስ ጥቆማ ትሰጣለች።
የፖሊስ ምርመራም የፈራችውን እውን አድርጎት ደውሎ ድምጿን ሰምቶ የሚዘጋው ግለሰብ ባሏ መሆኑን አረጋግጧል።
ፖሊስም ሚስቱን በማይታወቅ ስልክ ቁጥር በመደወል ሲያጨናንቅ የከረመውን ወጣት ስልክ መጥለፍን የሚከለክለውን የጃፓን ህግ ተላልፏል በሚል በቁጥጥር ስር አውሎታል።
ግለሰቡ በፖሊስ ሲጠየቅም “ሚስቴን እወዳታለው፤ የስልክ ጥሪውን አድርጌ ምንም ሳልመልስ እዘጋዋለው” ሲል ስልኳን መጥለፉን የሚያረጋግጥ ምላሽ ሰጥቷል ብሏል ኦዲቲ ሴንትራል በዘገባው።
በጃፓን በስራ ምክንያት የተራራቁና የሚቀኑ ባለትዳሮች አንዱ የሌላኛውን ስልክ የመጥለፍ ልምድ እንዳለ ይነገራል።
የአማጋሳኪ ፖሊስ ግን በቀን ከ100 ጊዜ በላይ የሚደውለው ግለሰብ ከሚስቱ ጋር በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖር መሆኑን በመጥቀስ፥ በአንድ ጣሪያ ውስጥ የሚኖሩ ባለትዳሮች በስልክ መጥለፍ ሲካሰሱ ይህ የመጀመሪያው ነው ብሏል።